ቤላሩስ የአውሮፓ ህብረት፤ ለስደተኞች የሰብአዊ ኮሪደር እንዲፈጥር ሀሳብ አቀረበች
የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ከጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር ተወያይተዋል
በጀርመን ጥገኝነት የጠየቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በፖላንድ ድንበር ላይ መስፈራቸው ይታወቃል
ቤላሩስ ከሰሞኑ ለተፈጠረው የስደተኞች ቀውስ የአውሮፓ ሕብረት ሰብዓዊ ኮሪደር እንዲፈጥር ሃሳብ ማቅረቧን አስታወቀች።
ሃሳቡ የቀረበው የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ከጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ውይይትም ለስደተኞች ሰብዓዊ ኮሪደር ሊፈጠር እንደሚገባ ሃሳብ ቀርቧል። የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረትም 2 ሺህ ስደተኞች ወደ ጀርመን እንዲሄዱ ዕድል ይፈጥራል ነው የጠባለው።
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት የፕሬስ ሴክሬታሪ ናታልያ ኢስሞንት በቤላሩስ 7 ሺህ ስተኞች መኖራቸውን ገልጸው 2 ሺ የሚሆኑት ደግሞ በድንበር ላይ እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ ከሰሞኑ በቤላሩስ የስደተኞች ቀውስ የተፈጠረ ሲሆን ከነዚህ ስደተኞች መካከል ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተስማሙት 400 ብቻ መሆናቸውንም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ተናግረዋል።
ሌሎቹ ስደተኞች ወደ ምዕራብ አውሮፓ በተለይም ወደ ጀርመን የሚወስደው የሰብአዊነት ኮሪደር እንዲሰጣቸው አጥብቀው መፈለጋቸውን ቀጥለዋል ነው የተባለው።
ስደተኞችን በተመለከተ በአውሮፓ ህብረት በኩል፣ ምንም ቁርጠኝነት እንደሌለም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ገልጸዋል። ሉካሼንኮ እና ሜርክል በሁለተኛው ውይይት ላይ እንደተስማሙት የአውሮፓ ህብረት በኤክስፐርት ደረጃ እንኳን እስካሁን ድርድር አለመጀመሩን ተናግረዋል።
ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከቤላሩስ ወደ ፖላንድ፣ ሊትዌኒያ እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ለመግባት እየሞከሩ ነው ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ ሕዳር 8፣ በጀርመን ጥገኝነት የጠየቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በፖላንድ ድንበር ላይ መስፈራቸው ይታወሳል።