ፒኤስጂ በኤሊዜ ቤተመንግስት የእራት ግብዣ ምባፔን ለማግባባት ይሞክር ይሆን?
ፕሬዝዳንት ማክሮን የኳታሩ ኢሚርና የፒኤስጂ ባለቤትን ጨምሮ የክለቡን ፕሬዝዳንትና ተጫዋቾች እራት ጋብዘዋል
የ25 አመቱ ፈረንሳዊ የውድድር አመቱ ሲጠናቀቅ ሪያል ማድሪድን ይቀላቀላል መባሉ ይታወሳል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኪሊያን ምባፔን ጨምሮ የፒኤስጂ ወሳኝ ተጫዋቾችን ዛሬ ምሽት እራት ጋብዘዋል።
በኤሊዜ ቤተመንግስቱ የእራት ግብዣ ላይ የኳታሩ ኢሚር እና የፒኤስጂ ክለብ ባለቤት ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ይገኛሉ ተብሏል።
የፓሪስ ሴንት ጀርሜን (ፒኤስጂ) ክለብ ፕሬዝዳንት ናስር አል ከሊፋም የማክሮን የግብዣ ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮንን ከኳታሩ ኢሚር ጋር በሚኖራቸው ቆይታ እስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ የተጀመረው ጥረትን በተመለከተ ይመክራሉ ነው የተባለው።
የፒኤስጂ ባለቤትና የክለቡ ፕሬዝዳንት በእራት ግብዣው የሚያገኙትን ኪሊያን ምባፔ በዚህ የውድድር አመት መጨረሻ የሚጠናቀቀውን ውሉን ለማራዘም በሚያስችሉ ጉዳዮች ሊመክሩ እንደሚችሉ ተገምቷል።
የፈረንሳዩ አርኤምሲ ስፖርት ባወጣው ዘገባ ግን የኳታሩ ኢሚርም ሆኑ የፒኤስጂ ፕሬዝዳንት ምባፔን ስለኮንትራት ማራዘም ጉዳይ የማነጋገር ሃሳብ የላቸውም ብሏል።
ክለቡ ፈረንሳዊው አጥቂ ወደ ሪያል ማድሪድ ለመዛወር ያሳለፈውን “የማይቀለበስ” ውሳኔ እንደሚያከብር ናስር አል ከሊፋ በሰጡት መግለጫ መግለጻቸውን በማስታወስ።
ምባፔ በ2022 ከፒኤስጂ ጋር ኮንትራቱን እንዲያራዝም የማግባባት ድርሻ የነበራቸው ፕሬዝዳንት ማክሮን በዛሬው የእራት ግብዣስ ምን ያደርጋሉ የሚለው ይጠበቃል።
ከፈረንሳይ የሚወጡ ዘገባዎች ግን በእራት ግብዣው ከምባፔ የኮንትራት ማደስ ጋር የተያያዘ አይደለም እያሉ ነው።
የ2018ቱ የአለም ዋንጫ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አባል የነበረው ምባፔ በ222 ሚሊዮን ዩሮ ከተቀላቀለው ብራዚላዊዉ ኔይማር ቀጥሎ በ94 ሚሊዮን ዶላር ሁለተኛ ውድ ተከፋይ ሆኖ ነበር በ2017 ከሞናኮ ወደ ፒኤስጂ የተቀላቀለው።
ፒኤስጂ አምስት የሊግ ዋን ድሎችን እንዲያገኝ ያደረገው ምባፔ በ291 ጨዋታዎች ተሰልፎ 244 ግቦችን አስቆጥሯል፤ የክለቡ የምንግዜም ግብ አስቆጣሪ በመሆንም እየመራ ነው።