ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቡርኪና ፋሶ የፈረንሳይ ወታደሮች ይውጡ ማለቷ እንዲብራራ ጠየቁ
ቡርኪና ፋሶ የፈረንሳይ ወታደሮች ሀገሪቱን በአንድ ወር ውስጥ ለቀው እንዲወጡ አዛለች
በቡርኪና ፋሶ ፀረ-ፈረንሳይ አመለካከት እያደገ መምጣቱ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ አሻራ አሳርፏል
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቡርኪና ፋሶ የፈረንሳይ ወታደሮች ይውጡ ማለቷ እንዲብራራ ጠየቁ።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እሁድ እለት ከቡርኪና ፋሶ አዲስ ወታደራዊ መሪ “ማብራሪያ” እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ማክሮን ይህን ያሉት ቡርኪና ፋሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፈረንሳይ ወታደሮች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟን ተከትሎ ነው።
ማክሮን በፓሪስ ለብዙኸን መገናኛዎች በሰጡት መግለጫ ከቡርኪና ፋሶ የተላከውን መልዕክት “ግራ አጋቢ” ብለውታል።
የቡርኪናፋሶ ብሄራዊ ብሮድካስቲንግ አርቲቢ እንደዘገበው ወታደራዊ መንግስቱ ባለፈው ረቡዕ የፈረንሳይ ጦር በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ቆይታ እንዲያቆም ወስኗል።
ማክሮን "ስለ ሪፖርቱ መጠንቀቅ ያለብን ይመስለኛል" በማለት በሩሲያ ሊፈጠር ይችላል ያሉትን ጣልቃ ገብነትና የመረጃ ክፍተት አለመኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ኢብራሂም ቴራኦሬ በመስከረም ወር ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ በቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በሆነችው ቡርኪና ፋሶ ፀረ-ፈረንሣይ አመለካከት እያደገ መምጣቱን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
አዲሱ መሪ ቴራኦሬ ከሌሎች ሀገራት በተለይም ከሩሲያ ጋር ለመስራት የበለጠ ፍላጎት አላቸው ነው የተባለው።
የፈረንሳይ አምባሳደር ከስልጣን እንዲወርዱና ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን የሚገኘው የፈረንሳይ የጦር ሰፈር እንዲዘጋ ተቃዋሚዎች በዚህ ወር በዋና ከተማዋ ሰልፍ ወጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ 400 የሚጠጉ የፈረንሳይ ልዩ ኃይል ወታደሮች ይገኛሉ።