ማክሮን በዩክሬን የሰላም እቅድ ዙሪያ ለመምከር ወደ ቻይና ሊያቀኑ ነው
ፕሬዝዳንቱ ቤጂንግ በሞስኮ ላይ ጫና በመፍጠር ጦርነቱ እንዲቆም የበኩሏን ድርሻ እንድትወጣ ጠይቀዋል
የቻይናን የሰላም እቅድ ዩክሬንም ሆነች ፈረንሳይ ቢደግፉትም ቤጂንግ ከሞስኮ ጎን ተሰልፋለች የሚለው ወቀሳ ቀጥሏል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቻይና ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ገለጹ።
ማክሮን ከአንድ ወር በኋላ በቤጂንግ የሚያደርጉት ጉብኝት ዋነኛ አላማም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ምክክር ማድረግ ነው ተብሏል።
ቻይና ባለፈው አርብ ሞስኮ እና ኬቭ አስቸኳይ የሰላም ንግግር እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ባለ12 ነጥብ የሰላም አማራጭ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም።
ኢማኑኤል ማክሮንም ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ አለምን በሁለት ጎራ የከፈለው ጦርነት በንግግር መቋጫ እንዲያገኝ ከጂንፒንግ ጋር እንደሚመክሩ ማሳወቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ቤጂንግ በሞስኮ ላይ ጫና በመፍጠር ጦርነቱ እንዲቆም የበኩሏን ድርሻ እንድትወጣ ማክሮን ጠይቀዋል።
ጦርነቱ እንዲቆምም ሆነ ሰላም እንዲሰፍን ግን ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን ምድር ማስወጣትና የዩክሬንን ሉአላዊነት ማክበር ይጠበቅባታል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የሰላም አማራጭ ያቀረበችው ቻይናም ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዳታደርግና ሞስኮ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎችን እንዳትጠቀም የማግባባት ስራ እንድትሰራም ጠይቀዋል።
የዩክሬንም ሆነ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንቶች የቻይናን የሰላም ጥሪ ቢቀበሉትም ቤጂንግ ገለልተኛ አቋም አላት ብለው ግን አያምኑም።
በህንድ የተሰባሰቡ የቡድን 20 አባል ሀገራት ሩሲያን የሚያወግዝ የጋራ መግለጫ እንዳያወጡ የተቃወመችው ቤጂንግ መሆኗንም ለዚህ የቅርብ ጊዜ ማስረጃ አድርገው ያቀርቡታል።
የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ በቻይና የሚያደርጉት ጉብኝትም የዚሁ ወገንተኝነቷ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚያነሱት።
የፑቲን የረጅም ጊዜ ወዳጅ ናቸው የሚባልላቸው ሉካሼንኮ ሞስኮ የሀገራቸውን ምድር ተጠቅማ በኬቭ ላይ ጥቃት እንድታደርስ አድርገዋል በሚል ይወቀሳሉ።
ሩሲያ እኛ ቤላሩስ በጥቅምት ወር 2022 የጋራ ቀጠናዊ ሃይል ማደራጀታቸውም አንድ አመት ያለፈውን ጦርነት እንዲረዝም ያደርጋል ስትል ኬቭ ደጋግማ መግለጿን ፍራንሥ24 አስታውሷል።
ቤጂንግም በምዕራባውያኑ ጥርስ ለተነከሰባቸው ሉካሼንኮ አስተዳደር የማደርገውን ድጋፍ አጠናክሬ እቀጥላለሁ ማለቷና ፕሬዝዳንቱ ከነገ በስቲያ የሚያደርጉት ጉብኝት የሃይል አሰላለፉን ያሳያል የሚሉ ተንታኞች አሉ።
ሩሲያ በበኩሏ በህንድ የተካሄደውን የቡድን 20 አባል ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያወኩት “አሜሪካ”፣ “የአውሮፓ ህብረት” እና የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ናቸው ብላለች።
ከትናንት በስቲያ አንደኛ አመቱን የያዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንዲቋጭ በቤላሩስ እና ቱርክ አንታሊያ የተደረጉት ጥረቶች ሳይሳኩ መቅረታቸው ይታወሳል።