“ዓለማችን በሁለት ልእለ ሀያል ሀገራት ልትመራ አይገባም”- ፕሬዝዳንት ማክሮን
ፈረንሳይ በአሜሪካና ቻይና መከከል በሚደረገው ፍትጊያ ሚዛናዊ ሀገር መሆኗን አስታውቃለች

ዓለማችን በሁለት ልእለ ሀያል ሀገራት ከተመራች ወደ ፍጥጫ ማምራቷ አይቀሬ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል
ዓለማችን በሁለት ልእለ ሀያል ሀገራት ልትመራ እንደማይገባ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ።
የፈርንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በእስያ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር መድረክ ላይ እንዳሉት ዓለማችን በሁለት ልዕለ ሀያል ሀገራት መመራቷ ስህተት እንደሚሆን ገልጸዋል።
አሜሪካ እና ቻይና የአለማችን ልዕለ ሀያል ሀገራት መሪ ለመሆን ትግል ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸው ባለፉት ዓመታት ከሁለቱም ጋር ሚዛናዊ ሀገር መሆኗን አክለዋል።
- የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ለምን አፍሪካ ቀንድ ላይ አይናቸውን ጣሉ?
- በኢራን ኑክሌር ጉዳይ ስምምነት ለመድረስ "አሁን ላይ ኳሱ በሜዳዋ ውስጥ" ያለው ኢራን ወሳኝ ነች-ኘሬዝደንት ማክሮን
ፕሬዝዳንት ማክሮን በንግግራቸው ላይ ባለፉት ዓመታት በዋሸንግተን እና ቤጂንግ መካከል መካረሮች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የታይዋን ጉዳይ፣ የሰብዓዊ መብት እና የንግድ ጦርነት ለቻይና እና አሜሪካ መካከል ላለው መካረር ምክንያቶች ናቸው።
የቡድን ሰባት ሀገራት የቻይናን ተጽዕኖ ለመመከት ከስድስት ወር በፊት በብሪታንያ ባደረገው ጉባኤ ከ300 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደቡ ይታወሳል።
በጀቱ በአፍሪካ እና እስያ ሀገራት ለመሰረተ ልማት እና ለንግድ ማሻሻያ እንደሚውል በወቅቱ መገለጹ አይዘነጋም።
ቻይና በበኩሏ የቡድን ሰባት ሀገራት ራሱን የተቀረው ዓለም ጠበቃ አድርጎ መሳሉ ስህተት መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚንስቴሯ በኩል አስታውቃ ነበር።