ማዳጋስካር ህጻናትን የሚደፍሩ ወንዶች ብልት እንዲቆረጥ የሚያዝ ህግ አዘጋጀች
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የማዳጋስካር ህግን ተችተዋል
በማዳጋስካር ህጻናትን የደፈሩ ወንጀለኞች በአምስት ዓመት እስር እየተቀጡ ናቸው
ማዳጋስካር ህጻናትን የሚደፍሩ ወንዶችን ብልት እንዲቆረጥ የሚያዝ ህግ አዘጋጀች፡፡
በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ የምትገኘው ማዳጋስካር ህጻናትን የሚደፍሩ ወንዶችን ብልት እንዲቆረጥ የሚያስገድድ ህግ አውጥታለች፡፡
ሀገሪቱ ህጻናቶቿን ከመደፈር አደጋ ለመጠበቅ ጥብቅ ረቂቅ ህግ ያዘጋጀች ሲሆን በዚህ ህግ መሰረት ደፋሪዎች ብልታቸው እንዲቆረጥ ይገደዳሉ፡፡
ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን የደፈሩ ወንዶች ብልታቸው በቀዶ ጥገና ሐኪም ተቆርጦ እንዲጣል ይደረጋል የተባለ ሲሆን ከ13 እስከ 18 ዓመት የሆናቸው ህጻናትን የደፈሩ ሰዎች ደግሞ በኬሚካ አማካኝነት ብልታቸው እንዲጎዳ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የማዳጋስካር ፍትህ ሚኒስትር ላንዲ በጉዳዩ ዙሪያ ለኤፍፒ በሰጡት ማብራሪያ በሀገሪቱ የሚደፈሩ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ይህንንም ለመከላከል የግድ ጠንካራ ህግ ማዘጋጀት አስፈልጎናል ብለዋል፡፡
በ2023 ብቻ 600 ህጻናት ተደፍረዋል ያሉት ሚኒስትሯ ላንዲ ጥፋተኛ የሆኑ ተከሳሾች በትንሹ ከአምስት ዓመት ጀምሮ እስር እየተላለፈባቸው ቢሆንም ለውጥ አለመምጣቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ተቋም አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ ጭካኔ እንጂ ጥፋተኞችን አያስተምርም ሲል አዲሱን የማዳጋስካር ህግ ተችቷል፡፡
የማዳጋስካር ፕሬዘዳንት ሁሉንም ሚኒስትሮች ከስራ አገዱ
ህጻናት ከጥቃት መጠበቅ አለባቸው፣ ደፋሪዎችም በህግ መጠየቅ አለባቸው ያለው አምንስቲ ኢንተርናሽናል ነገር ግን እርምጃው በሰዎች ላይ መገለልን እና የባሰ ጨካኝ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነውም ብሏል፡፡
ድርጅቱ አክሎም ወንጀሉን ሳይፈጽሙ ነገር ግን በብዙ ምክንያቶች ጥፋተኛ የሚባሉ ሰዎች ይኖራሉ በዚህ ጊዜ ህጉ ተግባራዊ ከተደረገ ሊቀለበስ የማይችል ጉዳት በሰዎች ላይ ሊደርስም ይችላል ሲል አሳስቧል፡፡
ይህ አከራካሪ ህግ አስገዳጅ ህግ ለመሆን ከግማሽ በላይ ያሉ ሂደቶችን አልፏል የተባለ ሲሆን የላይኛው ምክር ቤት ውሳኔ እና የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፊርማ ይቀረዋል ተብሏል፡፡