በ2016 ዓ.ም የነበሩ አበይት ክስተቶች ምን ምን ነበሩ?
የፓሪስ ኦሎምፒክ ውዝግብ፣ የሕዳሴው ግድብ ሀይል ማመንጨት እና የዜጎች መታገት በዓመቱ የነበሩ አበይት ክስተቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው
የአማራ ክልል ጦርነት፣ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው የወደብ ስምምነት እና የውጭ ሀገራት መገበያያ ገንዘቦች ምንዛሬ ጭማሪ ከዋነኞቹ ክስተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው
በ2016 ዓ.ም የነበሩ አበይት ክስተቶች ምን ምን ነበሩ?
ሁሌም አዲስ ዓመት ሲመጣ ተስፋን ይዞ መጣል፡፡ 2015 አልቆ ተራውን ለ2016 ሲለቅ ብዙዎች በአዲሱ ዓመት ለራሳቸው ቤተሰባቸው እና ሀገራቸው መልካም ምኞትን ተመኝተዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ መልካም እና መጥፎ ክስተቶችን እንደሚያስተናግድ የሚጠበቅ ቢሆንም እንደ ሀገር ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም የተፈጠሩ ዋና ዋና ክስተቶችን እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል፡፡
ጦርነት በአማራ ክልል
የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ ማለቱን ተከትሎ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ጦርነት በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች እንደቀጠለ ነው፡፡
ተመድ እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት እንዲቆም በተደጋጋሚ የጠየቁት ይህ ጦርነት ለንጹሃን ዜጎች ሞት፣ መሰደድ እና የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ለውድመት ዳርጓል፡፡
የወደብ ስምምነት እና የኢትዮጵያ-ሶማሊያ ውጥረት
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር ጥር ወር ላይ ያደረጉት የወደብ ስምምነት ሌላኛው እየተጠናቀቀ ባለው 2016 ዓ.ም ከነበሩ አበይት ክስተቶች መካከል አንዱ ነበር፡፡
ይህ ስምምነት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ከቀይ ባህር ተገላ የቆየችው ኢትዮጵያን ዳግም ወደ አካባቢው ይመልሳል ቢባልም በአንድ ወር ውስጥ ይተገበራል የተባለው ስምምነቱ 10 ወር አስቆጥሯል፡፡
በ2015 ዓ.ም የነበሩ አበይት ክስተቶች ምን ምን ነበሩ?
ከዚህ በተጨማሪም ሶማሊላንድ የግዛቴ አካል ናት የምትላት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችው ስምምነት ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በማቋረጥ ላይ ናት፡፡
ቱርክ በዚህ ስምምነት ምክንያት ግንኙነታቸው የሻከረው ኢትዮጵያን እና ሶማሊን በአንካራ በማደራደር ላይ ብትሆንም ሞቃዲሾ ከካይሮ ጋር ወታደራዊ ስምምነቶችን እና ትብብሮችን መፈጸሟን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ ተቀይሯል፡፡
ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ከሆኑን አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ብድር ለማግኘት ለዓመታት ስትመክር እና ብድሩን ለማግኘት የተለያዩ የህግ እና ፖሊሲ ማሻሻየዎችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ከነዚህ መካከል ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ መከተል መጀመሩ ዋነኛው ሲሆን ማሻሻያውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብር ከ100 ፐርሰንት በላይ ተዳክሟል፡፡
የ2016 ዓ.ም የመጨረሻ ቀን በሆነችው ጷግሜ 5 ላይ አንድ ዶላር በአማካኝ በ109 ብር በባንኮች እየተመነዘረ ይገኛል፡፡
የፓሪስ ኦሎምፒክ ውዝግብ
የኦሎምፒክ ውድድር በየ አራት ዓመቱ የሚካሄደው ሲሆን የዘንድሮው በፓሪስ አስተናጋጅነት ተካሂዷል፡፡
ኢትዮጵያ ከተሳታፊዎች መካከል አንዷ ስትሆን በአሸብር ወልደጊዮርጊዝ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ባልተለመደ መልኩ በአትሌቶች ምርጫ ጣልቃ መግባት፣ አትሌቶች ያላግባብ ከውድድር ተቀነስን እና በውድድሩ የውጤት ቀውስ መከሰት በዘንድሮው ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ታይተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአመራሮች፣ አሰልጣኞች እና አትሌቶች መካከል የተከሰተው ይህ ውዝግብ በወርቅ ሜዳሊያ ቁጥር መቀነስ ምክንያት ቅር መሰኘታቸውን የሚገልጹ አስተያየቶች የማህበራዊ ትስር ገጾችን ጨምሮ የሚዲያዎችን ትኩረት ስቦ አልፏል፡፡
ያለ ውጤት የተጠናቀቀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና የመንግስት ድርድር በታንዛኒያ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር እና ሕወሃት አመራሮች መከፋፈል፣ የኦነጉ በቴ ኡርጌሳ አመራር ግድያ፣የዜጎች በጉዞ ላይ እያሉ እና በመኖሪያ ቤታቸው መታገት፣ የባህርዳሩ የህጻን ሔቨን አስገድዶ መደፈር የፍርድ ቤት ችሎት ጉዳይ ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ ያደርግ የነበረውን በረራ ማቆም በ2016 ዓመት ከነበሩ ዋና ዋና ክስተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የእርስዎ ዋና የዓመቱ ክስተት ምን ነበር? አስተያየቶን ያጋሩን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!!