የአረብ ኢምሬትስን ወርቃማ ቪዛ ለማግኘት መስፈርቶቹ ምን ምን ናቸው?
አረብ ኢምሬትስ ለተመረጡ ሰዎች እስከ 10 ዓመት የሚዘልቅ የመኖሪያ ቪዛ ትሰጣለች
ሀገሪቱ በዓመት ለ152 ሺህ ሰዎች ወርቃማ ቪዛ በመስጠት ላይ ትገኛለች
የመካከለኛዋ ምስራቅ ሀገር የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በጎብኚዎች የምትወደድ እና በየዓመቱ የዓለም ባለጸጋዎችን በመሳብ ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡
ይህች ሀገር ከመደበኛው የቪዛ አገልግሎት በተጨማሪ ወርቃማ ቪዛ ወይም ጎልደን ቪዛ የሚል አገልግሎቶችን በመስጠት ላይም ትገኛለች፡፡
ወርቃማ ቪዛ ማለት ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ድረስ በሀገሪቱ ከተሞች መኖር የሚያስችል የመኖሪያ ፈቃድ ሲሆን ይህም የተለያዩ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ ይሰጣል፡፡
ይህን ወርቃማ ቪዛ ከሚያገኙ ሰዎች መካከል ወርሃዊ ደመወዛቸው 30 ሺህ ድርሃም እና ከዚያ በላይ የሆኑ የጤና ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ሌላኛው የዚህ ቪዛ ተጠቃሚዎች የሪል ስቴት አልሚዎች ሲሆኑ በአረብ ኢምሬትስ ውስጥ 2 ሚሊዮን እና ከዚያ በላይ ንብረት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ያለ ቪዛ በፓስፖርት ብቻ መግባት የሚችሉባቸው ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ስራ ፈጣሪዎችም ከ5 እስከ 10 ዓመት የሚቆየውን የወርቃማ ቪዛ ማመልከት የሚችሉ ሲሆን የፕሮጀክታቸው ሀሳብ 50 ሺህ ድርሃም እና ከዛ በላይ ዋጋ ሊኖረው ይገባል ተብሏል፡፡
ልዩ ችሎታ ያላቸው ባለ ተሰጥኦ ሰዎች ይህን ወርቃማ ቪዛ ለማግኘት ማመልከት ይችላሉ የተባለ ሲሆን በዚህ ዘርፍ ድምጻዊያን፣ አትሌቶች፣ ሳይንቲስቶች እና መሰል ሙያተኞች ዋነኛ የዚህ እድል ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ሰው ንዋይ ደበበ ከሰሞኑ በዚህ ዘርፍ የአረብ ኢምሬትስ ወርቃማ ቪዛን ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
ልዩ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎችም የአረብ ኢምሬትስን ወርቃማ ቪዛ የማግኘት መብት አላቸው የተባለ ሲሆን በዚህ እድል ለመጠቀም በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ 100 ዩንቨርስቲዎች እየተማሩ ያሉ እና ከተመረቁ ደግሞ 3 ነጥብ 5 እና ከዛ በላይ ውጤት ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል፡፡
በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት ውስጥ አምስት ዓመት እና ከዛ በላይ የሰሩ ባለሙያዎችም ከአምስት እስከ 10 ዓመታት ድረስ በአረብ ኢምሬትስ እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን ቪዛ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ አለም አቀፍ ወረርሽኝ ዘመቻዎች ላይ የተሳተፉ እና የተለየ ተጋላጭነት ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች ወርቃማውን ቪዛ ማግኘት ይችለሉ።