በ2023 የተከሰቱ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች
ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት 2023 60 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በርዕደ መሬት አደጋ ህይወታቸው ተቀጥፏል
በጎርፍ እና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ደግሞ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል
የፈረንጆቹ 2023 በተፈጥሮ እና የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትላቸው አደጋዎች ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል።
ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት 2023 ከ1 ሺህ 700 በላይ በሬክተር ስኬል ከ5 ነጥብ በላይ ሆነው የተመዘገቡ የርዕደ መሬት አደጋዎች ተመዝግበዋል።
በቱርክ፣ ሶሪያ፣ ሞሮኮና አፍጋኒስታን የደረሱት አደጋዎች የሺዎችን ህይወት ቀጥፈው በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ሃብትን አውድመዋል።
በ2023 የደረሱ ዋና ዋና የርዕደ መሬት አደጋዎችን እናስታውስዎ፦
የካቲት 2023 ቱርክና ሶሪያ
በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
የርዕደ መሬት አደጋው በቱርክ የ45 ሺህ 968: በሶሪያ ደግሞ የ7 ሺህ 259 ሰዎችን ህይወት መቀማቱ የሚታወስ ነው።
ከ345 ሺህ በላይ ቤቶችን ያወደመው አደጋ ከ15 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ለችግር ዳርጓል።
በ12 አመቱ የርስ በርስ ጦርነት ተደጋጋሚ ጉዳት ያስተናገዱ የሶሪያውያን ቤቶች ወደፍርስራሽነት ተለውጠው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፈታኝ ህይወትን ማሳለፋቸው አይዘነጋም።
መስከረም 2023 - ሞሮኮ
በሞሮኮ በስድስት አስርት ዓመታት ውስጥ እጅግ በጣም ከባድ ነው የተባለው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 8 ሆኖ ተመዝግቧል።
ከማራካሽ በ73 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው ርዕደ መሬት 3 ሺህ የጠጉ ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ ከ5 ሺህ በላዩን ለጉዳት ዳርጓል።
ሞሮኮ ርዕደ መሬቱ ያፈራረሳቸውን ከ19 ሺህ በላይ ቤቶች ዳግም ለመገንባትና ዜጎቿን መልሳ ለማቋቋም ከ11 ቢሊየን ዶላር በላይ በጀት መመደቧም የሚታወስ ነው።
ጥቅምት 2023 - አፍጋኒስታን
በምዕራባዊ አፍጋኒስታን ሄራት ከተሰኘችው ከተማ በ35 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 3 ሆኖ ተመዝግቧል።
በርዕደ መሬቱ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ህይወት አልፎ ከ9 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጎርፍ - ሊቢያ
የአየር ንብረት ለውጥ መዛባትና ድንገተኛ ተፈጥሯዊ አደጋዎች በ2023 የበርካታ ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል።
የሴቭ ዘ ቺልድረን መረጃ እንደሚያሳየው ሊጠናቀቅ የቀናት እድሜ የቀረው 2023 ከ240 በላይ ከአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ጋር የተያያዙ አደጋዎች ተመዝግበውበታል።
ከ2022 የ30 በመቶ ጭማሪ ያላቸው የጎርፍ፣ ሰደድ እሳት፣ የመሬት መንሸራተት እና አውሎንፋስ አደጋዎች ከ12 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት መቅጠፋቸውንም ጠቅሷል።
በሊቢያ በመስከረም ወር 2023 “ዳንኤል” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ማዕበል ያስከተለው የጎርፍ አደጋ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት መቀማቱ ይታወሳል።
በግሪክ፣ ቱርክ፣ ቡልጋሪያና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም በተመሳሳይ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ሰደድ እሳት - ሃዋይ
2023 የአለማችን ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበበት አመት ነው።
ከአልጀሪያ እስከ ቱኒዚያ፤ ከስፔን እስከ ፖርቹጋል ከግሪክ እስከ ፈረንሳይ የተዛመቱ የሰደድ እሳት አደጋዎችም ሺዎችን አፈናቅለው በርካታ ሰዎችን ለህልፈት ዳርገዋል።
በፖርቹጋል እስካሁን በእሳቱ እና በተፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያ 238 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ደን በእሳቱ መውደሙ ተገልጿል፡፡
በአሜሪካ ምስራቃዊ ክፍል የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬትን ያነደደ ሲሆን፥ ሃዋይን በተለይ ወደ ምድረ በዳነት ቀይሯል።
ከ2 ሺህ በላይ ቤቶችን ያወደመው አደጋ የ100 ሰዎችን ህይወት መቀማቱም የሚታወስ ነው።