![](https://cdn.al-ain.com/images/2023/12/28/243-124826-243-100232-252-210214-ap21158420051627-700x400-700x400_700x400.jpg)
የፈረንጆቹ 2023 በኢትዮጵያ ከልዩ ኃይሎች አደረጃጀት መፍረስ እስከ የቀይ ባህር ይገባኛል ጥያቄ ድረስ በርካታ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ተስተናግደዋል
ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት የፈረንጆቹ 2023 በኢትዮጵያ ከልዩ ኃይሎች አደረጃጀት መፍረስ እስከ የቀይ ባህር ይገባኛል ጥያቄ ድረስ በርካታ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ተስተናግደዋል።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ደግሞ በውጭ ከተከሰቱት ሁነቶች ቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል።
በአመቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የተከሰቱ ዋና ዋና ፖለቲካዊ ሁነቶችን እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።
የልዩ ኃይል መፍረስ እና የአማራ ክልል ግጭት
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሚያዝያ ወር የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀቶች እንዲፈርሱ ውሳኔ አስተላልፏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የውሳኔውን አስፈላጊነት አስመልክተው በወቅቱ ባወጡት መግለጫ ውሳኔው "ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" ሲባል "ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን" ተግባራዊ እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው የክልሎች ሚና ልዩ ኃይል ማደረጀት ሳይሆን የፖሊስ ኃይላቸውን አጠናክረው የአከባቢያቸውን ደህንነት መጠበቅ ነው ብለውም ነበር።
ይህ የመንግስት ውሳኔ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተቋጨ ከአምስት ወራት በኋላ በአማራ ክልል አዲስ ግጭት እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል።
የልዩ ኃይሉን የማፍረስ ውሳኔ የሚቃወሙ ሰልፎች በበርካታ የክልሉ ከተሞች ተካሂደዋል።
የፌደራል መንግስት ልዩ ኃይሎች እንደማይበተኑ እና የተሻለ ትጥቅ ወደሚያገኙበት የመንግስት የጸጥታ አደረጃጀቶች እንዲገቡ ምርጫ እንደተሰጣቸው ቢያብራራም፣ በክልሉ ያለው ተቃውሞ ወደ ትጥቅ ግጭት አምርቷል።
መንግስትም ወሳኔው እንዳይተገበር በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ወደ ስራ መግባቱን ይፋ አደረገ።
ይሁን እንጅ የትጥቅ ግጭቱ ከመቆም ይልቅ በበርካታ ቦታዎች ተባብሶ ቀጠለ።
መንግስትም የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በመደበኛ የህግ ማስከበር መቆጣጠር እንደማይችል በመግለጽ በክልሉ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሀምሌ ወር ማወጁ ይታወሳል።
ወደ ክልሉ በተሰማራው የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በብዙ ቦታዎች ግጭቶች ተቀስቅሰዋል።
አሁን ላይ መንግስት አብዛኛዎቹ የክልሉ አካባቢዎች ወደ ሰላም እንደተመለሱ ቢገልጽም፣ በገጠር አካባቢዎች ግን ግጭቶች መቀጠላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
የአሜሪካ መንግስት እና ተመድ በክልሉ ያለው ግጭት በድርድር እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።
መንግስትም ለሰላማዊ መፍትሄ ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም በምን መልኩ እንደሆነ በዝርዝር አልገለጸም።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
ልዩ ኃይል እንዲፈስ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል የመንግሰት የጸጥታ ኃይሎች የሰብአዊ ጥሰት መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ሪፖርት) አውጥቷል።
ኢሰመኮ መንግስት ካወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፊት እና በኋላ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሪፖርት አድርጓል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ መከላከያ ሰራዊትን በይፋ ከማሰማራቱ በፊት በጥቂት የአማራ ክልል ዞኖች ውስጥ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት መከሰቱን ባወጣው ሪፖርት ገልጾ ነበር።
ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ በነሀሴ ወር ባወጣው ሪፖርት በባህርዳር፣ በደብረ ብርሃን፣ በፍኖተ ሰላም ሰላማዊ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተገድለዋል ብሏል።
ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርቱ በሽዋ ሮቢት ከተማ የጸጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጭ መግደላቸውን የሚያሳይ መረጃ እንደደረሰው ገልጿል።
ኢሰመኮ ቀጥሎ ባወጣው መግለጫም አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ግጭት ውስጥ መሆናቸውን እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት መጨመሩን ገልጿል።
ኢሰመኮ በቅርቡ ባወጣው እና የሰብአዊ መብት ጥሰት መጨመሩን በገለጸበት ሪፖርቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ200 በላይ ሴቶች በመንግሰት የጸጥታ ኃይሎች ተደፍረዋል።
ኢሰመኮ በክልሉ በድሮን እና በከባድ መሳሪያ በርካታ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውንም ሪፖርት አድርጓል።
ተመድም በድሮን ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ይገባኛል ጥያቄ
የኢትዮጵያ መንግስት ያነሳው የቀይ ባህር ይገባኛል ጥያቄ እጅግ አነጋጋሪ የሆነ ርዕስ ነበር።
ባለፈው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመንግስት የመገናኛ ብዙኻን በተላለፈ ፕሮግራም ላይ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለመጠቀም መደራደር እንደምትፈልግ ይፋ አደርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በታሪክ የቀይ ባህር ባለቤት መሆኗን ገልጸው፣ አሁንም ቀይ ባህርን በሰላማዊ መንገድ መጠቀም እንደምትፈልግ መናገራቸው ይታወሳል።
የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ወደብ የምታገኝበትን መገንገድ በሰላማዊ መንገድ ካለመቻቹ፣ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ የደህንነት ችግር እንደሚያስክል አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በ2030ዓ.ም 150 ሚሊዮን ይደርሳል፣ ይህ ህዝብ ደግሞ የጄእግራፊ እስረኛ(ወደብ አልባ) ሆኖ መኖር አይችልም ሲሉ ነበር የተናገሩት።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ተከትሎ በተለይም የኤርትራ መንግስት ባወጣው መግለጫ ስለባህር በር እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱ ርዕሶች ግራ አጋቢ ናቸው ብሏል።
የኤርትራ መንግስት ለአትዮጵያ ቀጥተኛ መልስ ባይሰጥም፣ የባህር በር ጉዳይን ማንም እንዳይነካው ይጠንቀቅ ሲል አሳስቧል።
የህዳሴው ግድቡ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቅ
ኢትዮጵያ አራተኛውን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋን ባለፈው መስከረም ወር ይፋ አድርጋለች።
ነገርግን በግድቡ ጉዳይ ሲካሄድ የቆየው የሶስትዮሾ ድርድሩ እክል አጋጥሞታል።
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የኢትጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ አራተኛው ዙር የሶስትዮሽ የግድቡ ድርድር ሳይሳካ ቀርቷል።
ድርድሩ ያለስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ ግብጽ ባወጣችው መግለጫ ኢትዮጵያ ምንም አይነት የህግ እና የቴክኒክ ጉዳዮች ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆኗ አልተሳከም ብላለች።
ነገርግን ኢትዮጵያ ድርድሩ ያልተሳከም ግብጽ "የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብን በመያዟ" ነው የሚል ወቀሳ አቅርለች።
በኢትዮጵያ በኩል የግድቡ ተደራዳሪ የሆኑት ዶክተር ስለሺ በቀለ በድርቅ ጊዜ የሚኖረው የውሃ አለቃቀቅ እና አያያዝ ጉዳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያልተቻለበት ነጥብ መሆኑን ገልጸዋል።
ሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት
የሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት ከተጀመረ ስምነት ወራትን አስቆጥሯል።
ሀገሪቱን ለሶስት አስርት አመታት የመሩት አል በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ወታደራዊ ስልጣን በያዙት ጀነራል አል ቡርሃን እና መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት የሚያባራ አይመስልም።
በጦርነቱ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሲገሉ ከሰባት ሚሊዮን ሱዳናውያን በላይ ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
በጀነራል ሄሜቲ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች 70 በመቶውን የካርቱም ክፍል መቆጣጠራቸው ተገልጿል።
ድል እየቀናቸው ነው የተባሉት እነዚህ ኃይሎች በቅርቡ ከካርቱም በስተደቡብ ምስራቅ ያለችውን ዋድ መዳኒ ከተማ ቶጣጥረዋል።
ግጭቱን በንግግር ለመፍታት በተለይም አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ ያደረጉት ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
የእስራኤል- ሀማስ ጦርነት
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ድንበር በመጣስ በ50 አመታት ውስጥ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ እና ከባድ ጥቃት አደረሰ።
ሀማስ ይህን ጥቃት ያደረሰው ባለፈው ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ነው።
ሀማስ በሰነዘረው ጥቃት 1200 እስራኤላውያንን ገድሎ 240 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ ሸሸ።
በዚህ የተቆጣችው እስራኤል በሀማስ ላይ ጦርነት አወጀች።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ጦርነት ላይ ነን"በማለት ዘመቻውን አስጀመሩ።
እስራኤል በሀማስ ይዞታ በሆነችው ጋዛ ላይ በአየር እና በእግረኛ ጦር ባደረሰችው ጥቃት ከ20ሺ በላይ ፍልስጤማውያ መገደላቸውን የጋዛ ዛለስልጣናት ይናገራሉ።
በጦርነቱ አሜሪካ እስራኤልን ስትደግፍ፣ የየመኑ ሀውቲ አማጺ እና የሊባኖሱ የሄዝቦላ ለሀማስ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
የሌሎች ኃይሎች መሳተፍ ጦርነቱን ቀጣናዊ ያደርገዋል የሚል ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል።
አሁን ላይ እስራኤል ከጋዛ በተጨማሪ በሰሜን እና በቀይ ባህር በኩል የውጊያ ግንባር ተከፍቶባታል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በድሮን እና በሚሳይል ጥቃት ከመሰንዘር አልፈው ማንኛውም መርከብ ወደ እስራኤል እንዳይንቀሳቀስ እክል ፈጥረዋል፣ በርካታ መርከቦችም ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ጉዳዩ ያሳሰባት አሜሪካ፣ የመርከቦችን ደህንነት ለመጠበቅ 'ፕሮስፔሪቲ ጋርዲያን' የሚባል በርካታ ሀገራት የተሳተፉበት ግብረ ኃይል አቋቁማለች።
የሩሲያ ባክሙትን መቆጣጠር
22 ወራትን ባስቆጠረው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ዋግነር ግሩፕ በምስራቅ ዩክሬም የምትገኘውን የባክሙት ከተማን ተቆጣጠረ።
ባክሙትን ለመቆጣጠር የተካሄደው ውጊያ እጅግ ከባድ የሚባል ደም መፋሰስ የታየበት ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረችው የኔቶ ወደ ቀድሞ የሶቬት ሀገራት መስፋፋቱ ለደህንነቷ እንደሚያሰጋት በመግለጽ ነበር።
አራት የዩክሬን ግዛቶችንም ወደ ራሷ ግዛት መጠቅለሏን ሩሲያ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል። ዩክሬን በዚህ ጉዳይ ቁጣ አሰምታለች።
ሩሲያ እና ዩክሬን ለንግግር ዝግጁ እንደሆኑ ቢገልጹም የሚያቀርባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ግን የሚያቀራርቡ አልሆኑም።