ዓለም አዲስ ጦርነት የማስተናገድ እድል እንዳላትም ፎረሙ ጠቁሟል
በ2024 የዓለማችን ፈተና ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
ከቀናት በኋላ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ዓመታዊ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ የሚጠበቀው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም የ2024 አበይት የቢሆኔ ክስተቶችን ይፋ አድርጓል።
ፎረሙ ከ1ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ያሉ አመራሮችን እና ባለሙያዎችን ያሳተፈ የጥናት ውጤቱን ይፋ አድርጓል።
በዚህ ጥናት ከተሳተፉት ውስጥ 54 በመቶዎቹ በ2024 ዓመት አዲስ አለመረጋጋት ሊከሰት ይችላል ብለው ያምናሉ ተብሏል።
እንዲሁም 30 በመቶ ተሳታፊዎቹ ደግሞ ዓለማችን ካለመረጋጋት ባለፈ የከፋ ችግር ይከሰታል ብለው እንደሚያምኑም ተገልጿል።
ከባድ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ተከስቶ በርካቶችን ሊጎዳ ይችላል የተባለ ሲሆን የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት እና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች ይከሰታልም ተብሏል።
ሌላው እነዚህ የዓለም ቢዝነስ፣ ቴክኖሎጂ እና ማህበራዊ ተቋማት መሪዎች በ2024 ችግር ይሆናል ካሏቸው ጉዳዮች መካከል ጉዳይ ሐሰተኛ መረጃ ዋነኛው ነው።
ሌላኛው የዓለማችን ስጋት ይሆናል የተባለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ቴክኖሎጂ ሲሆን የበይነ መረብ መንታፊዎችም በተያዘው የ2024 ዓመት በስጋትነት ተይዟል።
የሀያላን ሀገራት በስራኤል እና ዩክሬን የጀመሩት መካረር ሊዛመት ይችላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን በታይዋን አዲስ ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችልም ተሰግቷል።
የነዳጅ ዋጋ መናር ሌላኛው በዚሁ ዓመት ዓለም የሚያሳስብ ጉዳይ ሲሆን በዚህ ምክንያትም የመጓጓዣ ዋጋ ሊያሻቅብ እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ሊጎዳው ይችላልም ተብሏል።