ቶዮታ በዓለም ገበያ የተሸጡ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎቹን ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ አዘዘ
ራቫ4፣ ኮሮላ፣ ሌክሰስ እና ካምሪ የተሰኙ ተሽከርካሪዎች የደህንነት ችግር አለባቸው ከተባሉት መካከል ዋነኞቹ ናቸው
ሌላኛው የጃፓን ኩባንያ ሱዙኪ ጥሩ የገበያ እድል ሊያገኝ እንደሚችል ተገልጿል
ቶዮታ በዓለም ገበያ የተሸጡ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎቹን ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ አዘዘ።
ዓለም አቀፉ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ቶዮታ ከ2020 እስከ 2022 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተመረቱ ተሽከርካሪዎች የደህንነት ችግር አለባቸው ተብሏል።
ኩባንያው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተመረቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ከኤርባግ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለባቸው ተደርሶበታል ብሏል።
ድርጅቱ በተለይም ኮሮላ፣ ራቫ4፣ አቫሎን፣ ሌክሰስ፣ ካምሪ፣ ሴና ሀይብሪድ፣ አርኤክስ 350፣ ኢኤስ250፣ ኢኤስ350 የተሰኙ የ2020 እና 2022 ላይ የተመረቱት የኤርባግ ችግር እንዳለባቸው አስታውቋል።
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት ተሽከርካሪዎች ያላቸው ሰዎች ኤርባጋቸውን እንዲያረጋግጡ እና ችግር ካጋጠማቸው እስከ ቀጣዩ የካቲት ወር ድረስ እንዲመልሱለት ቶዮታ ጥሪ አቅርቧል።
የቶዮታ ተሽከርካሪዎች ችግር እንዳለባቸው የታወቀው የጃፓን ትራንስፖርት ሚኒስቴር በሀገሪቱ ተሽከርካሪ እምራች ኩባንያዎች ላይ ባደረገው ምርመራ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ ምርመራ መሰረት ከቶዮታ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ ዳይሀትሱ በተሰኘው ኩባንያ ላይም ተመሳሳይ ችግር ታይቷልም ተብሏል።
ይህን ተከትሎም የቶዮታ ኩባንያ አክስዮን ዋጋ ቅናሽ አሳይቷልብየተባለ ሲሆን ሌላኛው የጃፓን ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጥሩ የገበያ እድል እንደሚያገኝ ተገልጿል።
ከ87 ዓመት በፊት ኪቺሮ ቶዮታ በተባለ ግለሰብ የተመሰረተው ቶዮታ የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ አሁን ላይ በዓመት 10 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማምረት ላይ ይገኛል።
ከ360 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ቶዮታ ኩባንያ 300 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሀብት እንዳለው የኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ያስረዳል።