በ2024 የነበሩ ዋና ዋና ስፖርታዊ ሁነቶች የትኞቹ ናቸው?
በተጠናቀቀው የፈረንቹ 2024 ከአውሮፓ ዋንጫ እስከ ኦሎምፒክ ትላልቅ ስፖርታዊ ሁነቶች ተከናውነውበታል
አመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የተለያዩ ክብረወሰኖችን በማሳካት በግሉ ስኬታማ የሆነበት ነበር
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 አመት በርካታ የአለምን ቅርጽ የቀየሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሁነቶች የተስተናገዱበት ነበር፡፡
በተመሳሳይ በስፖርቱ ዓለም በርካቶች የሚመለከቷቸው ተወዳጅነት ያላቸው አለም አቀፋዊ ስፖርታዊ ሁነቶችም በዚሁ አመት ተስተናግደዋል፡፡
የፓሪስ ኦሎምፒክ፣ የአውሮፓ ዋንጫ፣ የአርጄንቲና የኮፓ አሜሪካ 16ኛ ጊዜ ድል፣ የባላንዶር ሽልማት፣ የሳኡዲ አረብያ የ2034 የአለም ዋንጫ አዘጋጅነት እና የክርሰቲያኖ ሮናልዶ ክብረወሰኖች ከሚጠቀሱት ዋና ዋና የስፖርት አጋጣሚዎች መካከል ናቸው፡፡
-የፓሪስ ኦሎምፒክ
ከመክፈቻው ጀምሮ አወዛጋቢ የነበረው የ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ የተለያዩ አዳዲስ ሁነቶች የተስተናገዱበት ነበር፡፡
ለየት ያለ የመክፈቻ ትርዒትን ለማሳየት ሰፊ ዝግጅት ደረገችው ፓሪስ ከስታድየም ውጪ 100 ጀልባዎች በሴን ባህር ላይ በታዋቂዎቹ ኖትረዳም እና ሉቭረ በኩል አትሌቶች የሀገራቸውን ሰንደቅአላማ በማውለብለብ አልፈዋል፡፡
በመክፈቻው ዕለት የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች የሊዮናርዶ ዳቬንቺን የእየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው እራት ስዕልን ተጠቅመው ላስተላለፉት መልእክት በመላው አለም በሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍ ያለ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡
አዘጋጆቹ የስዕሉን አቀመማጥ በመጠቀም ታሪኩን የግሪክ አማልክት እና ከሌሎች ከሀይማኖቱ ጋር የማይገናኙ ውክልናዎችን ለማንጸባረቅ ተጠቅመውበታል፡፡
የካቶሊክ እምነት ተከታዮችን ጨምሮ የክርስትና አማኞች በመክፈቻው ላይ በተላለፈው መልዕክት ቁጣቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም አዘጋጆቹ ፕሮግራሙ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ለፈጠረው ቅሬታ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶች የተሳተፉበት 33ኛው የበጋ ኦሎምፒክ ውድድር በ32 አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች ከሀምሌ 19 እስከ ነሃሴ 5 2016 ዓም ድረስ ተካሂዷል፡፡
በውድድሩ በ10 ሺህ ሜትር ሁለቱም ጾታ፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር ፣ በ800 ሜትር ፣ በማራቶን እና ሌሎች ርቀቶችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተወከለችው ኢትዮጵያ የተጠበቀውን ያህል ውጤት አላስመዘገበችም፡፡
ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ በአንድ ወርቅ እና በ3 ብር ከአፍሪካ አልጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካን በመከተል 4ኛ ፣ ከአለም ደግሞ 47ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡
ለ17 ቀናት ከ206 ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች የተሳተፉበት የፓሪስ ኦሎምፒክ አሜሪካ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ የበላይ የሆነችበት ነበር
40 የወርቅ፣ 44 የብር እና 42 የነሃስ ሜዳልያዎችን ያገኘችው አሜሪካ ከቻይና ጋር በወርቅ ሜዳልያ እኩል ብትሆንም በብርና ሜዳልያዎች ብዛት በመብለጥ የፓሪስ ኦሎምፒክ የሜዳልያ ሰንጠረዥን በበላይነት አጠናቃለች።
በመድረኩ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የ25 አመቷ አልጄሪያዊት ቦክሰኛ ጾታ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡
በውድድሩ የመጀመሪያ ግጥሚያ ጣሊያናዊቷን ተፎካካሪ በ46 ሰከንድ በበቃኝ ያሸነፈችው ኢማን ካሊፍ በጾታዋ ሁኔታ ዙርያ በውድድሩ መነጋገርያ ሆና መቆየቷ ይታወቃል፡፡
ኢማን በፍጻሜው ጨዋታ ቻይናዊቷን ንግ ሊዩን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ውድድሩን ጨርሳለች፡፡
-17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ
በጀርመን አዘጋጅነት የተካሄደው 17ኛው የአውሮፓ በአመቱ ከተከናወኑ ግዙፍ አለምአቀፋዊ ስፖርታዊ ሁነቶች መካከል ተጠቃሹ ነው፡፡
በአራት አመት አንዴ የሚካሄደውና ከአለም ዋንጫ ቀጥሎ በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት የአውሮፓ ዋንጫ 24 ብሄራዊ ቡድኖች ተሳትፈውበታል፡፡
ለአህጉራዊ ውድድር አጠቃላይ ሽልማት 357 ሚሊየን ዶላር የተዘጋጀ ሲሆን አሸናፊው ሀገር ደግሞ 30 ሚሊየን ዶላር ተቀብሏል፡፡
በ10 የጀርመን ከተሞች የተካሄደው ውድድር መክፈቻው በአሊያንዝ አሬና የዋንጫ ጨዋታው ደግሞ በኦሎምፒያ ስታዲየም ተካሂዷል፡፡
በስድስት ምድቦች በወጣው ድልድል አዘጋጇ ጀርመን፣ እንግሊዝ ፣ ስፔን እና ፈረንሳይ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት አግኝተው ነበር፡፡
በርቱ ፉክክር እና ያልተጠበቁ ውጤቶች በተስተናገዱበት ውድድር ስፔን አዘጋጇን ሀገር ጀርመን በሩብ ፍጻሜ በመጣል ለዋንጫው ፉክክር ከእንግሊዝ ጋር ቀርባለች፡፡
ለአንድ ወር ያህል የተካሄደው የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ የስፔን ብሔራዊ ቡድን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮን ሆኖ አጠናቋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በተከታታይ አራት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ስፔን የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን የ17 ዓመቱ ስፔናዊ ላሚን ያማል ምርጥ ወጣት ተጨዋች በመሆን ተሸላሚ ሆኗል።
በውድድሩ ጠንካራ ቡድን መስርተው ምንም ጨዋታ ሳይሸነፉ ለዋንጫ የደረሱት ስፔኖች የእንግሊዝን ለ60 አመታት የቆየ የዋንጫ ርሀብ ለማስታገስ አልፈቀዱም።
-የኮፓ አሜሪካ እና የአርጄንቲና 16ኛ ድል
በአሜሪካ አዘጋጅነት የተካሄደው የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አህጉራዊ የእግርኳስ መድረክ (ኮፓ አሜሪካ) በአርጀንቲና አሸናፊነት ተደምድሟል።
በሚያሚ ሃርድ ሮክ ስታዲየም ኮሎምቢያን የገጠመችው አርጀንቲና ላውታሮ ማርቲኔዝ በጭማሪ ስአት (112ኛ ደቂቃ) ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በማሸነፍ 16ኛ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫዋን አንስታለች።
በውድድሩ አምስት ጎሎችን ያስቆጠረው ማርቲኔዝ የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ሆኗል።
አርጀንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በኮፓ አሜሪካ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ባይሆንም ሁለተኛ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫውን አሳክቷል።
እስከ34 አመቱ በአለማቀፍ ውድድሮች ዋንጫ ያላነሳው ሜሲ፥ ከ2021 ወዲህ ሶስት ዋንጫዎችን ከሀገሩ ጋር አሳክቷል (ሁለት ኮፓ አሜሪካ እና አንድ የአለም ዋንጫ)።
-የ2024 ባላንዶር እጩ እና አሸናፊዎች
ኮከብ የእግር ኳስ ተጨዋቾች የሚሸለሙበት ባላንድኦር በ2024 30 የእግር ኳስ ተጫዋቾች በእጩነት አቅርቧል
በዝርዝሩ ውስጥ ከፈረንጆቹ 2003 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የ8 ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ እና የ5 ጊዜ የባላንድኦር አሸናፊው ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሳይካተቱ ቀርተዋል።
በሌላ በኩል ናይጄሪያዊው የአታላታ ተጨዋች አዴሞላ ሉክማን በዚህ አመት በባሎን ዶር እጩ ውስጥ የተካተተ ብቸኛው የአፍሪካ ተጨዋች ሲሆን የ 17ዓመቱ ስፔናዊው የባርሴሎና የፊት መስመር ተጨዋች ላሚን ያማል በባሎን ዶር እጩዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተተ በታሪክ በእድሜ ትንሹ ተጨዋች መሆን ችሏል።
በፍራንስ ፉትቦል አዘጋጅነት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ስፔናውያኑ ሮድሪ ሄርናንዴዝ በወንዶች እንዲሁም አይታና ቦማቲ በሴቶች የባሎን ዶር አሸናፊዎች መሆን ችለዋል።
የስፔን ብሄራዊ ቡድን እና የማንችስተር ሲቲ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ሮድሪ የሪያል ማድሪዱን ቪኒሺየስ ጁኒየርን በመብለጥ የ2024 የባሎንዶር ሸናፊ መሆን የቻለ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ ሪያል ማድሪዶች የፈረንሳዩን የሽልማት ስነ ስርዓት በመቃወም ሳይታደሙ ቀርተዋል።
-የሳኡዲ አረብያ የ2034 አለም ዋንጫ አዘጋጅነት
የአለማቀፉ የእግርኳስ ማህበር (ፊፋ) ሳኡዲ አረቢያ የ2034ቱን የአለም ዋንጫ ለማስተናገድ በብቸኝነት ያቀረበችውን ጥያቄ በይፋ ተቀብሏል፡፡
ሳኡዲ ከአስር አመት በኋላ የሚካሄደውን የወንዶች የአለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ከ200 በላይ ተወካዮች ድምጽ እንደሰጧት ነው የተገለጸው።
ስፔን፣ ፖርቹጋል እና ሞሮኮ ደግሞ የ2030ውን የአለም ዋንጫ እንደሚያዘጋጁ በይፋ ተገልጿል።
ሳኡዲ አረቢያ የ2034ቱን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት በብቸኝነት ጥያቄውን ካቀረበች በኋላ ዝግጅቷን ጀምራለች።
ለውድድሩ ከሚያስፈልጋት 15 ስታዲየሞች ውስጥ የአራቱን ግንባታ እያካሄደች ትገኛለች።
-የክርሰቲያኖ ሮናልዶ ክብረወሰኖች
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ 2024 በግሉ ስፖርታዊ እና ከስፖርት ውጭ የሆኑ ክበረወሰኖችን ያሳካበት አመት ነበር፡፡
“እኔ ክብረወሰኖችን አላሳድድም ክብረወሰኖች ራሳቸው ያሳድዱኛል” ያለው የ39 ዓመቱ ሮናልዶ፤ አሁንም አዳዲስ ክብረወሰኖችን በእጁ ማስገባቱን ቀጥሏል።
ከእነዚም መካከል
-በተከታታይ ለ21 ዓመታት ለብሔራዊ ቡድኑ ግብ ማስቆጠር የቻለ በታሪክ የመጀመሪያው ተጨዋች
-ለሳዑዲ አረቢያው አል ናሰር የሚጫወተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የዘንዶሮ የሳዑዲ ፕሮ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን፤ በ31 ጨዋታ 35 ጎሎች መረብ ላይ በማሳረፍ በሳውዲ ሊግ በአንድ የውድድር አመት ብዙ ጎል በማስቆጠር ደረጃውን በቀዳሚነት ይዟል
-በሁሉም ውድድሮች ከ900 በላይ ጎሎችን በማስቆጠር በአለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው ሰው
-የዩቲዩብ ገጹን ባስተዋወቀ በ90 ደቂቃዎች ውስጥ 1.69 ሚሊየን ተከታዮችን በማግኘት አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል።
-በሁሉም በማህበራዊ ትስስር ገጾችም አንድ ቢሊየን ተከታዮችን በማፍራት ቀዳሚው ሰው ነው
2024 የእግርኳስ አፍቃሪዎች በርካታ የሜዳ ላይ ጥበበኞችን የተሰናበቱበት አመት ነበር
ብራዚላዊው ማሪዮ እና የጀርመን ብሄራዊ ቡድንና የባየርሙኒክ ፈርጥ ፍራንዝ ቤከንባወርም በ78 አመቱ በሞት የተለየው በጥር ወር 2024 ነበር።
የጣሊያን የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪው ጂጂ ሪቫ እና ሌላኛው የሀገሩ ልጅ ሳልቫቶር ስኪላቺ (ቶቶ) በ2024 ህይወታቸው ካለፉ የእግርኳስ ከዋክብት ውስጥ ይገኙበታል።