ዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛ የተባለውን የጦር እስረኞች ልውውጥ አደረጉ
ሀገራቱ በዚህኛው ዙር 300 እስረኞችን የተለዋወጡት በአረብ ኤሜሬትስ አሸማጋይነት መሆኑ ተሰምቷል
ሩሲያ እና ዩክሬን አዲሱ የፈረንጆቹ አመት ከመግባቱ በፊት በአይነቱ ከፍተኛ የተባለውን የጦር እስረኞች ልውውጥ አድርገዋል
ሩሲያ እና ዩክሬን አዲሱ የፈረንጆቹ አመት ከመግባቱ በፊት በአይነቱ ከፍተኛ የተባለውን የጦር እስረኞች ልውውጥ አድርገዋል፡፡
ለ3 አመታት በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ጎረቤት ሀገራት በዚህኛው ዙር 300 የሚጠጉ እስረኞችን መለዋወጣቸው ተዘግቧል፡፡
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ የሩሲያ የጦር እስረኞች በቤላሩስ ድንበር ላይ ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሩሲያ መጓጓዛቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው አረብ ኤሜሬረትስ በተለያዩ ዙሮች እስረኞችን ለማስለቀቅ ለምታደርገው የተሳካ የሽምግልና ስራ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በይፋዊ የቴሌግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "የዜጎቻችን ከሩሲያ ምርኮ መመለስ ሁልጊዜ ጥሩ ዜና ነው፤ በዛሬው እለትም 150 ዩክሬናውያንን ወደ ቤት ማምጣት ችለናል" ብለዋል፡፡
በማህበራዊ ገጻቸው ፕሬዝዳንቱ ባጋሩት ጽሁፍ የዩክሬን ባንዲራን የያዙ ወታደሮች በአውቶብስ ውስጥ ተቀምጠው የሚያሳይ ምስል አያይዘዋል፡፡
በአሁኑ ዙር ከተለቀቁት መካከል በ2022 በማሪዮፖል ደቡባዊ ወደብ የተያዙ ወታደሮች፣ የተለያዩ የግንባሩ መኮንኖች እንዲሁም ሁለት ሲቪሎች እንደሚገኙበት ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አረብ ኤሜሬቶች በ10 ዙሮች በአጠቃላይ 2484 እስረኞችን በሁለቱም በኩል ማስለቀቅ መቻሏን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ ገልጻለች፡፡
ድርድሩ እንዲሳካ የሁለቱን ሀገራት ፈቃደኛነት ያወደሰው ሚኒስቴሩ ለመጨረሻ ጊዜ ሀምሌ ላይ በአቡዳቢ አደራዳሪነት 190 እስረኞች መለቀቃቸውን በመግለጫው አክሏል፡፡
በቀጣይም ሀገራቱ ከሚገኙበት ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲወጡ እና ወደ ዘላቂ ጦርነት ማቆም ድርድር ይቀርቡ ዘንድ አቡዳቢ የገነባቸውን እምነት እንደምትጠቀምበት አስታውቃለች፡፡