ዩትዩብ አዲስ ካስተዋወቀው የአጫጭር ቪዲዮ አገልግሎት እንዴት ገንዘብ መስራት ይቻላል?
ከቲኪቶክ ጋር ፉክክር ውስጥ የገባው ዩ ትዩብ ተጠቃሚዎች ከአጫጭር ቪዲዮዎች ትልቅ ገንዘብ የሚያገኙበት አማራጭ አቅርቧል
ዩ ትዮብ በአዲሱ የቪዲዮ አገልግሎት “45 በመቶ የማስወታቂያ ገቢን ቪዲዮ ለሚሰሩ ሰዎች አጋራለሁ” ብሏል
ከቲክቶክ ጋር ከፍተኛ ውድድር ውስጥ የገባው ዩ ትዩብ የይዘት ፈጣሪዎች ከአጫጭር ቪዲዮዎች ትልቅ ገንዘብ የሚያገኙበት አዲስ አማራጭ ይዞ መምጣቱን ከሰሞኑ አስታውቋል።
ዩ ትዮብ ከቲክ ቶክ ጋር ለመፎካር በሚል 1 ደቂቃ ርዝመት ያላቸው አጫጭር ቪዲዮዎችን ለመጫን የሚያስችል አገለግሎት በፈረንጆቹ 2020 ላይ ያስተዋወቀ ሲሆን፤ በዚህም በወር እስከ 1.5 ቢሊየን የሚደርሱ ተመልካቾችን ማፍራት መቻሉ ተነግሯል።
የጎግል ኩባያ አካል የሆነው ዩ ትዩብ አዲስ ባስተዋወቀው የአጫጭር ቪዲዮ አማራጭ ከፍተኛ ተከታይ ላላቸው የይዘት ፈጣዎች የማስታወቂያ ገቢን እንደሚያጋርም ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።
- ቲክ ቶክ በኢንተርኔት በመጎብኘት ጎግልን በመብለጥ የዓለማችን ቀዳሚ ገጽ ሆነ
- ቲክቶክ ለወደድነው ቪዲዮ ገንዘብ ቲፕ የምናደርግበት አማራጭ እየሞከረ መሆኑን አስታወቀ
የዩ ትዩብ ፕሮዳክት ኦፊሰር ኔይል ሞሃን፤ ኩባያው ከቀጣይ የፈረንጆቹ 2023 ጀምሮ ከአጫጭር ቪዲዮዎች ማስታወቂያ የሚገኝ ገቢን ቪዲዮውን ከጫኑ የይዘት ፈጣዎች ጋር እንደሚጋራ አስታውቀዋል።
በዚህም ዩ ትዩብ ከአጫጭር ቪዲዮ ማስታወቂያዎች ከሚያገኘው ገቢ 45 በመቶውን ቪዲዮውን ከጫኑ የይዘት ፈጣዎች ጋር እንደሚጋራም ተናግረዋል።
ከአጫጭር ቪዲዮዎች እንዴት ገንዘብ መስራት ይቻላል?
በአጫጭር ቪዲዮዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የዩትዩብ የይዘት ፈጣሪዎች ከፈረንጆቹ 2023 መጀመሪያ ጀምሮ ገቢ ለማግኘት እንዲችሉ ለዩ ትዩብ ፓርትነርሺም ፕሮግራም ማመልከት ይችላሉ ተብሏል።
ታዲያ ለዚህ ማመልከት የሚችሉት 1 ሺህ ሰብስክራይበር ያላቸው እና በ90 ቀናት ውስጥ 10 ሚሊየን ጊዜ መታየት የቻሉ መሆናቸውንም ዩ ትዩብ በብሎግ ፖስ ላይ አስታውቋል።
ኦሪጂናል ወይም የራስ ፈጠራ የሆኑ ቪዲዮዎችን መስራት እና መጫን (ቲክቶክ መሰል የቪዲዮ መጋሪያዎች ላይ የተጫኑ ቪዲዮወችን በዩትዩብ አጭር ቪዲዮ ላይ ተቀባይነተ የለውም)።
እድሜ ከ13 ዓመት በላይ መሆን፣ ለዩትዩብ ፓርትነርሺፕ የተዘገበ ሀገር ውስጥ መሆን እና የዩ ትዩብን የሞኒታይዜሽን ፖሊሲ እና መመሪያዎችን በጠበቀ መልኩ መስራት ገንዘብ ለመስራት ብቁ ያደርጋል ተብሏል።