ክትባቱ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጡ የውጤታማነት መመዘኛ መስፈርቶችን ያሟላ የመጀመሪያው የወባ ክትባት ነው ተብሏል
ለወባ በሽታ የሚሆን ክትባትን ለማዘጋጀት ባደረጉት ምርምር ውጤት ማግኘታቸውን የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች አስታወቁ፡፡
ተመራማሪዎቹ እጩ ክትባት መሆኑን በተናገሩለት R21/Matrix-M ክትባት ላይ አደረግን ባሉት ሁለተኛ ምዕራፍ የላቦራቶሪ ምርምር ክትባቱ 77 በመቶ ያህል በሽታውን ለመዋጋት የሚያስችል አቅም እንዳለው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ይህ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጡ የክትባቶችን የማዳን የመቶኛ ምጣኔ መስፈርቶችን የሚያሟላ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
R21/Matrix-M እ.ኤ.አ በ2019 ከግንቦት እስከ ነሃሴ ባሉት የክረምት ወራት ውስጥ ወረርሽኙ ሊከሰት ከሚችልባቸው ወራት ቀደም ብሎ በቡርኪና ፋሶ በ450 ህጻናት ላይ በተለያየ መጠን ተሞክሯል፡፡
በሙከራውም ከፍ ያለ የክትባቱን መጠን ያገኙ 77 በመቶ አነስ ያለ ያገኙት ደግሞ 71 በመቶ ያህል በሽታውን ለመከላከል ችለዋል በዩኒቨርስቲው ይፋዊ ገጽ እንደሰፈረው ምርምሩን የተመለከተ ገለጻ፡፡
ከዚያ ወዲህም የተለያዩ አቅሙን ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በቀጣይም የምዕራፍ 3 የላቦራቶሪ ሙከራዎች በ4 ሺ 800 ህጻናት ላይ በአራት የአፍሪካ ሃገራት የሚደረጉ ይሆናልም ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተጨማሪ ምርምሮች ቢያስፈልጉም እንኳ ግኝቱን በተስፋ ሰጪነት አድንቀዋል፡፡
አር ቲ ኤስ፣ኤስ (RTS, S) የተሰኘ ሌላ ተስፈኛ ዕጩ ክትባትም አለ በምዕራፍ ሶስት የሙከራ ሂደት ላይ ያለ፡፡
ክትባቱ በታንዛኒያ የተሞከረ ሲሆን በሌሎች የከሰሃራ በታች ሃገራት በበጎ ፈቃደኞች ላይ መሞከሩ እንደሚቀጥልም ተነግሯል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ RTS, S እስካሁን ዓመቱን ሙሉ ወባ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች በሚገኙ ከ650 ሺ በላይ ህጻናት ላይ ተሞክሯል ነው ያሉት፤ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውን በመጠቆም፡፡
በገዳይነታቸው ከሚታወቁ የሰው ልጅ በሽታዎች መካከል ወባ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ የሚጠቀስ ነው፡፡
በየዓመቱ የ400 ሺ ሰዎች በዋናነትም የህጻናት ህይወት በወባ ምክንያት ይቀጠፋል፡፡
የወረርሽኙን ስርጭት በመግታት ረገድ ተስተውለው የነበሩ ውጤቶች አሁን አሁን እየቀነሱ መምጣቸውም ነው የሚነገረው፡፡
ባለፉት 10 ገደማ ዓመታት ከመቶ የሚልቁ የወባ ክትባት ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ የክትባት ውጤታማነት መመዘኛ መስፈርት ሳያሟሉ ስለመቅረታቸው ነው የሚነገረው፡፡