“ቀን ቀን ለኢትዮጵያ የሚሠሩ የሚመስሉ፣ ሌሊት ሌሊት በኢትዮጵያ ላይ የሚዶልቱ አሉ…እነርሱ ከውጭ ጠላቶቻችን በላይ ጠላቶቻችን ናቸው”-መንግስት
ምከር ቤቱ “በያዝነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግድባችንን ሞልተን ኃይል ማምረት እንጀምራለን” ሲልም አስታውቋል
የብሔራዊ ደህንነት ምከር ቤት ባወጣው መግለጫ “መጀመሪያ በውስጣችን ያሉትን ባለ ሁለት ቢላዋዎች እናጸዳለን” ብሏል
ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ለውጥ ጎዳና የገባነው በመንገዱ ላይ “ችግሮች አይገጥሙንም በሚል እሳቤ አልነበረም” ያለው መግለጫው ፣ ነገር ግን “ችግሮቹ እንኳን እርስ በእርስ እየተጓተትን ቀርቶ አንድ ሆነንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ድምጥማጣቸው የሚጠፋ አይደለም” ሲል አክሏል።
“ሀገራችን ያሉባት ችግሮች ምንም ያህል እንደ ምድር አሸዋ ቢበዙ ፈጽሞ ከዜጎቿ አቅም በላይ እንደማይሆኑ ጽኑ እምነት አለን። የሚፈቱትም ተነጣጥለን ሳይሆን በአንድነትና በትብብር እንደሆነ ገና ከጅምሩ አሳውቀናል” ብሏል መግለጫው፡፡
“የጠላቶቻችን ፍላጎት በጉዞአችን መሐል ወድቀን ግባችንን ሳናሳካ እንድንቀር ነው። በጋራ ቆመን ያጸናነው ቤታችን ፈራርሶ ወደ ትቢያነት ሲቀየር ማየት እንደሚሹ በመግለጽ እኛ ደግሞ ለዚያ የተመቸን ሆነንላቸዋል”ም ብሏል።
አሁን ባለንበት ጊዜ “ሦስት ወሳኝ ዓላማዎቻችንን በጽናት ማሳካት ይኖርብናል ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ፣ በመጀመሪያ አንድ ወር ያህል ጊዜ የቀረውን ምርጫ ውጤታማ እናድርገው” ብሏል።
ሁለተኛ ከምርጫው ጎን ለጎን ግድባችንን ባቀድነው መንገድና ጊዜ መንባትና ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወን አለብን ያለ ሲሆን “የትኛውንም ዓይነት ጫና ተቋቁመን፤ የውስጥና የውጭ ፈተናዎቻችንን አልፈን እንሞላዋለን። ኢትዮጵያን መውደዳችንን የምናሳየው የኢትዮጵያን ጉዞ በማቀላጠፍ እንጂ በማደናቀፍ አይደለም። በእሳት ላንቃ ውስጥ እያለፍንም ቢሆን ማድረግ ያለብንን ማድረግ አለብን። በያዝነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግድባችንን ሞልተን ኃይል ማምረት እንጀምራለን” ሲል መግለጫው አትቷል።
በየአቅጣጫው የምናየው “የወገኖቻችን አሲቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ቤትና ንብረት ማውደም፣ ነውጥና ሸፍጥ ሁሉ በሀገር ውስጥ ብቻ የተመረተ አይደለም” ሲልም ነው መግለጫው ያስቀመጠው። ቀጥሎም በመግለጫው እንደተገለጸው፡ አብዛኛው ጥፋት በውጭ ተመርቶ በሀገር ውስጥ የሚገጠም ጥፋት ነው ግጭቱንና ጥፋቱን ከውጭ አስመጥተው በሀገር ውስጥ የሚገጣጥሙት የእፉኝት ልጆች ናቸው። በዚህ ዓመት መጀመሪያ የእፉኝቶችን ዋና መፈልፈያ አፍርሰነዋል። ከዚህ በፊት ፈልፍሎ እዚህና እዚያ የጣላቸው ግልገሎቹ ግን አሁንም ይቀራሉ። የትኛውንም ዓይነት የብሔርና የእምነት ስም ቢይዙ ፤ ከየትኛው የውጭ ኃይል የሚረዱትን ገንዘብና መሣሪያ ቢጨብጡ ኢትዮጵያን ይፈትኗት ይሆናል እንጂ አያሸንፏትም።
“መጀመሪያ በውስጣችን ያሉትን ባለ ሁለት ቢላዋዎች እናጸዳለን። ቀን ቀን ለኢትዮጵያ የሚሠሩ የሚመስሉ፤ ሌሊት ሌሊት በኢትዮጵያ ላይ የሚዶልቱ አሉ። እነርሱ ከውጭ ጠላቶቻችን በላይ ዋነኞቹ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ አጥር ላይ ተቀምጠው፣ አሸናፊውን አይተው፣ ከተመቻቸው ሊገቡ፣ ካልተቻቸው ሊሸሹ የሚያስቡ መኖራቸውን አውቀናል። ወቅቱ የምርጫ ነውና መምረጥ አለብን። ወይ እነርሱን እናጸዳለን ወይ ኢትዮጵያን አሳልፈን እንሰጣለን። የኛ ምርጫ ኢትዮጵያን ለእነርሱ ስንል መሠዋት ሳይሆን፤ እነርሱን ለኢትዮጵያ ስንል መሠዋት ነው” ብሏል የብሔራዊ ደህንነት ምከር ቤቱ መግለጫ።
ምክር ቤቱ በመግለጫው ተከታዩን መልዕክትም አስተላልፏል፡
በአጠቃላይ ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ለማድረግ፤ ግድባችንን በታቀደለት መንገድ ገንብተን ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ለማከናወን፤ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ታድገን ወደሚገባት ደረጃ ለመውሰድ እንድንችል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃትና በብስለት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን። ቆም ብለን እናስብ፤ ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያን እናስቀድም።
በፌዴራልና በከልል የጸጥታ አካላት፣ ተቀናጅታችሁና ተናብባችሁ በመሥራት የኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያውያንን ሰላምና ደኀንነት እንድታስጠብቁ እናሳስባለን፡፡ የሚደረጉ ማናቸውም የፖለቲካና የመብት እንቅስቃሴዎች ይደገፋሉ። የትግላችን ውጤቶች ናቸውና፡፡ እነዚህ የመብትና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ግን ኢትዮጵያን እንዲያናውጡ አንፈቅድም። ፖለቲካዊ ጨዋታውን ከጨዋታ ሜዳ ውጭ ለማድረግ ለሚፈልጉት ኃይሎች፣ ትእግሥታችን ማለቁን በዚሁ አጋጣሚ ልንነግራቸው አንፈልጋለን። ሁሌም እንደምንለው፤ በጽናትም እንደምናምንበት፣ ለኢትዮጵያ ፈተና ብርቋ፣ ድል ማድረግም ሰበር ዜናዋ አይደለም። ከዚህ በላይ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ይሄንን አልፋ ነገ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ማሸነፏ ላይቀር እንዳታሸንፍ ሲታገሉ የኖሩትን ትታዘባቸዋለች፤ በታሪክ ሂደትም ትቀጣቸዋለች። እርሷ ግን ወጥመዱን በጣጥሳ፣ ሰንኮፉን ነቃቅላ፣ አዚሙን አስወግዳ ያሰበችበት ትደርሳለች።
ኢትዮጵያ እስካሁን የቆየችውም ወደፊትም የምትቆየውም፣ በእኛ በመስዕዋት ልጆቿ ደምና አጥንት ነው። ዛሬ እኛ የምንከፍለው ዋጋ፣ ነገና ከነገወዲያ ሀገራችንን ወደማይቀለበስ የብልጽግና ከፍታ ላይ እንደሚያደርሳት ምንም ጥርጥር የለውም።