የማላዊውን ምክትል ፕሬዝዳንት አሳፍሮ ደብዛው ጠፍቶ የነበረው አውሮፕላን ተከስክሶ ተገኘ
ምክትል ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ የሞቱ የቀድሞ ሚኒስትር የቀብር ስነስርአትን ለመታደም በጉዞ ላይ እያሉ ነው አደጋው የተከሰተው
በአደጋው ምክትል ፕሬዝዳንቱን ጨምሮየዘጠኝ ሰዎች ህይወት አልፏል
የማላዊውን ምክትል ፕሬዝዳንት አሳፍሮ ሲበር የነበረው እና ትላንት መጥፋቱ የተነገረው አውሮፕላን ተከስክሶ ተገኝቷል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሳውሎስ ቺሊማ እና ሌሎች 9 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው ወታደራዊ አውሮፕላን ከራድር ውጭ መሰወሩን ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳነት ላዛሩስ ቻክዌራ የነፍስ አድን ፍለጋ መጀመሩን አስታውቀው ነበር፡፡
በቺካንጋዋ ጫካ ለመጨረሻ ጊዜ የታየውን አውሮፕላን ለማግኘት የሀገሪቱ መከላከያ ሲያደርግ በነበረው ፍለጋ ከአደጋው ማንም ሳይተርፍ አውሮፕላኑ ሙሉለሙሉ ወድሞ አግኝቶታል፡፡
የ51 አመቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቺሊማ በቅርቡ የሞቱ የቀድሞ የመንግስት ሚንስትር የቀብር ስነስርአትን ለመታደም በጉዞ ላይ እያሉ ነው አደጋው ያጋጠማቸው፡፡
አውሮፕላኑ ከዋና ከተማዋ ሊሎንገዋ ተነስቶ በምዝዙ አውሮፕላን ማረፊያ ከአንድ ሰአት በኋላ ለማረፍ አቅዶ ሲጓዝ የነበረ ቢሆነም በአስቸጋሪ የአየር ጸባይ ሁኔታ ምክንያት ጉዞውን አቋርጦ ወደ ዋና ከተማዋ እየተመለሰ ባለበት በቺካንጋዋ ጫካ ተከስክሷል፡፡
ከ2014 ጀምሮ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩት ቺሊማ በማላዊያን በተለይ በወጣቱ ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቻክዌራ በአደጋው እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው ለዜጎቻቸው እና ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የነበሩት ቺሊማ በቀጣይ አመት በሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እጩ ይሆናሉ ተብለው ይጠበቁ ነበር፡፡