ሁለት የማሌዢያ ባህር ኃይል ሄሊኮፕተሮች አየር ላይ ተጋጩ
በሄሊኮፕተር ግጭት አደጋው የ10 ሰዎች ህይወት አልፏል
የሄሊኮፕተር ግጭት አደጋ ያጋጠመው በመደበኛ ልምምድ ላይ እያሉ ነው ተብሏል
በማሌዢያ ሁለት የባህር ኃይል ሄሊኮፕተሮች በወታደራዊ ትርኢት ልምምድ ለይ እያሉ መጋጨታቸው ተነግሯል።
የሄሊኮፕተር ግጭት አደጋው ዛሬ ጠዋት ላይ ያጋጠመ ሲሆን፤ በአደጋውም 10 የማሌዢያ የባህር ኃይል አባላት ህይወት ማለፉ ነው የተነገረው።
ሄሊኮፕተሮቹ የተጋጩት የፊታችን ቅዳሜ ለሚከበረው የሀገሪቱ ባህር ኃይል ለሚያቀርበው ወታደራዊ ትርዒት በልምምድ ላይ እያሉ እንደሆነም የማሌዢያ የባህር ኃይል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አደጋው የተከሰተው ዛሬ ጥዋት በምዕራባዊ የፔራክ ግዛት በሉሙት የባህር ኃይል ጣቢያ መሆኑን የባህር ሃይሉ ገልጿል።
"በሄሊኮፕተሩ ውስጥ የነበሩ ሁሉም የበረራ አባላት በቦታው መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ማንነታቸውን ለመለየት ወደ ሉሙት የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ወታደራዊ ሆስፒታል መላካቸውንም የባህር ሃይሉ አስታውቋል።
በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በርካታ ሄሊኮፕተሮች በመብረር ላይ እያሉ ከእነሱ ውስጥ ሁለቱ ክንፋቸው ተጋጭተው መሬት ላይ ተከስክሰዋል።
የአካባቢው ፖሊስም በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል እውነተኛ ነው ሲል አረጋግጧል።
የማሌዢያ የባህር ኃይል የአደጋውን መንስዔ እንደሚመረምር አስታውቋል።
የማሌዢያ የመከላከያ ሚኒስትር ሞሃመድ ካሊድ ኖርዲን፤ በአየር ላይ የተጋጩት ሄሊኮፕተሮች የፊታችን ቅዳሜ ለሚከበረው የማሌዢያ ሮያል ኔቪ 90ኛ ዓመት የመስረታ በዓል ልምምድ ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል።
በአደጋው ህይወታቸው ያለፈው ሁሉም የበረራ አባላት እድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች መሆኑን እና ማንነታቸውን ለመለየት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።