ማሊ፤ ፈረንሳይ የአየር ክልሌን በመጣስ ታጣቂዎችን እየደገፈች ነው ስትል ከሰሰች
ባማኮ ታጣቂዎቹ የመሣሪያ እና የመረጃ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ስትል ለተመድ አቤት ብላለች
የፈረንሳይ ጦር ከማሊ መውጣቱ ይታወሳል
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ፤ ፈረንሳይ የአየር ክልሌን በመጣስ ለታጣቂዎች ጦር መሳሪያ እያቀረበች ነው ስትል ከሰሰች።
የማሊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁኔታውን በማስመልከት ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጽፏል።
በደብዳቤው የሃገሪቱ የአየር ክልል በዚህ ዓመት ብቻ ከ50 ለሚበልጡ ጊዜያት በዋናነትም በፈረንሳይ ወታደራዊ ድሮኖች፣ የጦር ሄሊኮፕተሮች እና የጦር ጄቶች መጣሱን ገልጿል እንደ ሮይተርስ ዘገባ።
ይህ ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የደህንነት መረጃዎችንና ጦር መሳሪያዎችን በማቅረብ ማሊን ለማተራመስ የሚደረግ እንደሆነም ነው ደብዳቤው የሚያትተው።
ሆኖም ፈረንሳይ ክሱን አስተባብላለች። ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በሽብተኝነት ከፈረጁት ታጣቂዎች ጋር በቀጥታም ሆነ ሆነ በተዘዋዋሪ ያደረገችው ድጋፍ እንደሌለም ነው ባማኮ የሚገኘው ኤምባሲዋ የገለጸው።
ፈረንሳይ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በሚል ወታደሮቿን በማሊ ላለፉት 9 ዓመታት አሰማርታ ነበር።
ሆኖም ከአዲሱ የኮሎኔል አሲሚ ጎይታ መንግስት ጋር ስምምነት ባለመኖሩ ምክንያት ከቀናት በፊት ሙሉ በሙሉ ማሊን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።
ማሊ በባማኮ የነበሩትን የፈረንሳይ አምባሳደርን ከሀገሯ ያባረረች ሲሆን በማሊ የሰፈረው የፈርንሳይ ጦር እንዲወጣም ጠይቃ ነበር።
ይሄንን ተከትሎም ፈረንሳይ በማሊ በሶስት ካምፖች ሰፍሮ የነበረው የፈረንሳይ ጦር በተለያዩ ዙሮች ስታስወጣ የቆየች ሲሆን በዛሬው ዕለት የመጨረሻው ዙር ወታደሮች ከዘጠኝ ዓመት ቆይታ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሀገሪቱን ለቆ ወጥቷል።