ኒጀር፣ ማሊ እና ቢርኪናፋሶ ከኢኮዋስ አባልነት መውጣታቸውን አስታወቁ
በወታደራዊ መንግስት የሚመሩት ሀገራት “ኢኮዋስ በውጭ ሃይሎች ተጠምዝዞ ከፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ተንሸራቷል” ብለዋል
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ሶስቱን ሀገራት ከአባልነት ማገዱ ይታወሳል
ኒጀር፣ ማሊ እና ቢርኪናፋሶ ከኢኮዋስ አባልነት መውጣታቸውን አስታወቁ።
ሶስቱ በወታደራዊ መንግስት የሚመሩ ሀገራት ባወጡት መግለጫ በ1975 ከመሰረቱት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ በይፋ መውጣታቸውን ጠቁመዋል።
ሀገራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ ኢኮዋስ “በውጭ ሀይሎች ተጠምዝዞ ከቀደሙት የቡድኑ መስራቾች የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ተንሸራቷል” ብለዋል።
“ኢኮዋስ የተመሰረተበትን መርህ በመካድ ለአባል ሀገራቱ እና ህዝቦቻቸው ስጋት ሆኗል”ም ነው ያሉት።
15 ሀገራትን ያቀፈው ቡድን በአባል ሀገራቱ የሚንቀሳቀሱ አክራሪ ሃይሎችን ሁከት ማስቆም እንዳቃተውም ጠቅሰዋል።
የኢኮዋስ እና የሶስቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር የጀመረው በማሊ በ2020፣ በቡርኪናፋሶ በ2022 በኒጀር ደግሞ በሃምሌ ወር 2023 የመንግስት ግልበጣ ከተደረገ በኋላ ነው።
ኢኮዋስ ሀገራቱ ወደ ዴሞክራሲያዊና ሲቪል አስተዳደር እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥሪ ተቀባይነት ባለማግኘቱም ሶስቱም ሀገራት በጊዜያዊነት ከአባልነት ማገዱና የተለያዩ ማዕቀቦችን መታሉ ይታወሳል።
ኒጀር፣ ማሊና ቡርኪናፋሶ “የኢኮኖሚ ማህበረሰቡ ወሳኝ አባላት ናቸው” ያለው ኢኮዋስ፥ በሀገራቱ ያሉ ውጥረቶች እንዲረግቡና በፖለቲካዊ ንግግሮች ልዩነቶች እንዲፈቱ እንደሚፈልግ አስታውቋል።
ሶስቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከኢኮዋስ መውጣታቸውን ቢያሳውቁም በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ለቀጣይ 12 ወራት ለስብስቡ ደንብ ተገዥ የመሆን ግዴታ አለባቸው ብሏል ፍራንስ 24 በዘገባው።
ኢኮዋስ በሀገራቱ ላይ ማዕቀቦችን የመጣልና ካስፈለገም ወታደሮችን ሊያስገባ እንደሚችል ተገልጿል።
የቀድሞ ቅኝ ገዥያቸውን ፈረንሳይ ወታደሮች ያስወጡትና ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት የመሰረቱት ኒጀር፣ ማሊና ቡርኪናፋሶ በመስከረም ወር 2023 የጋራ ወታደራዊ ጥምረት ለመመስረት መስማማታቸው አይዘነጋም።
የማሊና ቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪዎች ምርጫ በማካሄድ ስልጣናቸውን ለማስረከብ ቃል ቢገቡም ሽብርተኞችን መዋጋትን ቅድሚያ እንሰጣለን በሚል ምክንያት አራዝመውታል።
ኒጀርም ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ በጥቂቱ ሶስት አመት ያስፈልገኛል ማለቷ የሚታወስ ነው።