የግድያ ሙከራው የተፈጸመው ዛሬ ረፋድ በኢድ አል አድሃ በዓል ላይ ነው
በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት የማሊው ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ኮለኔል አስሚ ጎይታ የግድያ ሙከራ ተፈጸመባቸው።
የግድያ ሙከራውን የፈጸሙት ሁለት የታጠቁ ሰዎች ቢላዋ ከያዘ ሶስተኛ ሰው ጋር በመሆን ዛሬ ረፋድ እንደሆነ ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የግድያ ሙከራው ኮለኔል አስሚ ጎይታ በማሊ መዲና ባማኮ ባለ አንድ መስጊድ ውስጥ የኢድ አል አድሃ በዓል ለማክበር በተጠራ የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል።
በዚህ የግድያ ሙከራ ላይ ፕሬዚዳንቱ ይጎዱ አይጎዱ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን፤ ፕሬዘዳንቱ ወደ ሌሎች ስፍራ መወሰዳቸው ዘገባው አክሏል።
የማሊ ዕምነት ሚኒስትር ማማዱ ኮኔ እንዳሉት አንድ ሰው ፕሬዚዳንቱን ለመግደል አስቦ እንዳልተሳካለት ተናግረዋል።
የመስጊዱ ዳይሬክተር በበኩላቸው ጥቃት ፈጻሚው ግለሰብ ፕሬዚዳንቱን ለማጥቃት አስቦ ቢሰነዝርም ሌላ ሰው መቁሰሉን ተናግረዋል።
ማሊ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ከጽንፈኛ አክራሪዎች የሚሰነዘርባትን የሽብር ጥቃት ለመመከት የተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎችን በማካሄድ ላይ ስትሆን ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀርም ተመሳሳይ ችግሮች አሉባቸው።
የ38 ዓመቱ ኮለኔል አስሚ ጎይታ ባሳለፍነው ነሀሴ በፕሬዘዳንት አቡበከር ኬታ ላይ መፈንቅለ መንግስት ፈጽመው ጊዜያዊ መንግስት እንዲቋቋም አድርገው ነበር።
ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳድሩን በማፍረስ እራሳቸውን የማሊ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አድርገው መሾማቸው ይትወሳል።
በዚህ ድርጊታቸውም አፍሪካ ሀብረትን ጨምሮ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ማሊን ከአባልነት አግደዋል።
ዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማትም በማሊ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እስኪመጣ ድረስ የገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርጉ አስጠንቅቀዋል።