በፓሪሱ ውድድር 44ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ቼፕቴጊ ከፈረንጆቹ 2021 ወዲህ ኬንያ ውስጥ ግድያ የተፈጸመባት ሶስተኛዋ አትሌት ሆናለች
ኡጋንዳዊቷን አትሌት በመግደል የተከሰሰው ግለሰብ መሞቱ ተዘገበ።
በኡጋንዳዊቷ አትሌት ርብቃ ቼፕቴጊ ላይ ጋዝ ደፍቶ በእሳት እንድትያያዝ በማድረግ ገድሏል በሚል የተከሰሰው የቀድሞ የፍቅር አጋሯ በጥቃቱ ወቅት በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ መሞቱን ህክምና ሲከታተል የነበረበት ሆስፒታል በዛሬው እለት ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ በተካሄደው የማራቶን ውድድር የተሳተፈችው የ33 አመቷ ቼፕቴጊ ከሳምንት በፊት በደረሰባት ጥቃት 75 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ክፍሏ ቃጠሎ ደርሶበታል። ቼፕቴጌ ጥቃት ከደረሰባት ከአራት ቀናት በኋላ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።
የቀድሞ የፍቅር አጋሯ ዲክስን ኒይዴማ ማራንጋች በትናንትናው እለት መሞቱን ቼፕቴጊ ስትታከም የነበረችበት እና ህይወቷ ያለፈበት በምዕራብ ኬንያ የሚገኘው የሞይ የማስተማሪያ እና የሪፈራል ሆስፒታል ቃለ አቀባይ ዳንኤል ላንጋት ተናግረዋል።"በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ህይወቱ አልፏል" ብሏል ላንጋት።
በፓሪሱ ውድድር 44ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ቼፕትጊ ከፈረንጆቹ 2021 ወዲህ ኬንያ ውስጥ ግድያ የተፈጸመባት ሶስተኛዋ አትሌት ሆናለች።
የእሷ ግድያ በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የቤት ውስጥ ጥቃት አጉልቶ ያሳየ ነው ተብሏል።
የመብት ተሟጋቾች የኬንያ ሴት አትሌቶች በሽልማት ያገኙትን ገንዘብ ለመበዝበዝ በሚፈልጉ ወንዶች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው ይላሉ። የኬንያ መንግስት የ2022 መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ እድሜያቸው 15-49 የሚሆኑ ኬንያውያን ሴቶች አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በሀገሪቱ በተለይ ያገቡ ሴቶች ጥቃት ከፍ ያለ ነው። ይኸው መረጃ እንደሚያሳየው ካገቡ ሴቶች ውስጥ 41 በመቶ የሚሆኑት የጥቃት ሰላባ ሆነዋል።
የተመድ ሴቶች ጥናት በ2023 ያወጣው መረጃ በአለም ደረጃ በ11 ደቂቃ ልዩነት አንድ ሴት የቤተሰብ አባሏ በሆነ ሰው ትገደላለች።