የማሊ ፕሬዚዳንት ከአንድ ሳምነት በፊት የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸው ነበር
በማሊው ፕሬዘዳንት ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸመው ግለሰብ ህይወቱ አለፈ።
በማሊ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት ኮለኔል አስሚ ጎይታ ባሳለፍነው ማክሰኞ ዕለት የአረፋ በዓልን ለማክበር በአገሪቱ መዲና ባማኮ በሚገኝ መስጊድ ውስጥ እያሉ በአንድ ግለሰብ በቢላዋ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸው ነበር።
ፕሬዘዳንቱ ከዚህ የግድያ ሙከራ የተረፉ ሲሆን የፕሬዘዳንቱ ጠባቂዎች ጥቃት አድራሹን ግለሰብ በተሽከርካሪ ገፍተውት እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ ግለሰብ በሆስፒታል ህክምና ላይ እያለ ህይወቱ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን፤ የጸጥታ ሃይሎች ስለ ግለሰቡ አሟሟት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ዘገባው አክሏል።
ይህ ግለሰብ በወቅቱ በተሽከርካሪ የደረሰበት ጉዳት ለሞት የሚያበቃ እንዳልነበር የተገለጸ ቢሆንም፤ በግለሰቡ አሟሟት ዙሪያ ምርመራ በመደረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ማሊ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ከጽንፈኛ አክራሪዎች የሚሰነዘርባትን የሽብር ጥቃት ለመመከት የተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎችን በማካሄድ ላይ ስትሆን ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀርም ተመሳሳይ ችግሮች አሉባቸው።
የ38 ዓመቱ ኮለኔል አስሚ ጎይታ ባሳለፍነው ነሀሴ በፕሬዘዳንት አቡበከር ኬታ ላይ መፈንቅለ መንግስት ፈጽመው ጊዜያዊ መንግስት እንዲቋቋም አድርገው ነበር።
ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳድሩን በማፍረስ እራሳቸውን የማሊ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አድርገው መሾማቸው ይታወሳል።
በዚህ ድርጊታቸውም አፍሪካ ሀብረትን ጨምሮ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ማሊን ከአባልነት አግደዋል።
ዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማትም በማሊ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እስኪመጣ ድረስ የገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርጉ አስጠንቅቀዋል።