ልዩልዩ
በሞዛምቢክ የሌላ ሰው መራቢያ አካል ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ተጠርጣሪ ተያዘ
በሀገሪቱ የሞቱ ሰዎችን አካል መጠቀም ብዙ በረከቶችን ያስገኛል ተብሎ ይታሰባል
የሰው ጭንቅላት እና የወንድ መራቢያ ይዞ የተገኘው ግለሰብ ከዚህ በፊትም ልምድ እንዳለው ተገልጿል
በአፍሪካዊቷ ሞዛምቢክ አንድ ግለሰብ በፕላስቲክ ውስጥ የሰው ልጅ ጭንቅላት እና የወንድ ሰው መራቢያ አካል ይዞ ሲንቀሳቀስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡
በሀገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ውስጥ በምትገኘው ናማታንዳ ከተማ ጎዳናዎች ላይ የነበሩ ህጻናት አንድ ግለሰብ የሰው ልጅ ጭንቅላት እና የወንድ መራቢያ አካል በፕላስቲክ ውስጥ አድርጎ ሲጓዝ በማየታቸው ጉዳዩን ለፖሊስ መጠቆማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፖሊስም በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ባደረገው ማጣራት ግለሰቡ ሰውን በመግደል የሰውነት ክፍሉን በመቁረጥ ይዞ በመጓዝ ላይ እንደነበር ተገልጿል፡፡
- ኡጋንዳ ከሌባ ላይ ሰርቀዋል የተባሉ 10 ፖሊሶችን በቁጥጥር ስር አዋለች
- “ኢየሱስን ለማየት ተራቡ” በሚል 58 ሰዎች ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገው ፓስተር ተያዘ
ተጨማሪ ምርመራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው የተባለ ሲሆን ተጠርጣሪው የያዛቸውን የሰውነት አካሎች ለመሸጥ ማሰቡ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ተጠርጣሪው ለፖሊስ ከዚህ በፊት ሶስት ሰዎችን እንደገደለ ማረጋገጡ የተነገረ ሲሆን የሰውነት ክፍላቸውንም እንደሸጠ ተገልጿል፡፡
የተገደሉ የሰውነት ክፍሎችን ማን እንደሚገዛ እና ስለ ግድያዎቹ አመቻቾች ተጨማሪ ምርመራ በመካሄድ ላይ መሆኑን የግዛቲቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግሯል ተብሏል፡፡
በሞዛምቢክ የሞቱ ሰዎች የሰውነት አካልን መጠቀም ጽኑ ህመሞችን ይፈውሳል፣ ረጅም ጊዜ በህይወት ለመኖር ያግዛል እና ሌሎች በረከቶችን ያስገኛል የሚል ዕምነት እንዳለ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡