በፔሩ ከ200 በላይ ቀኝ እግር ጫማዎችን የሰረቁት ተጠርጣሪዎች እየተፈለጉ ነው
የጫማ መደብሩ ባለቤት ጫማዎቹ ካልተገኙ 13 ሺህ ዶላር ኪሳራ ይገጥመኛል ብሏል
ዘራፊዎቹ ከመደብሩ ሲወጡ በደህንነት ካሜራ በመቀረጻቸው ፖሊስ አፈላልጎ ለመያዝ ጥረት እያደረገ ነው
በፔሩ ከ200 በላይ ቀኝ እግር ጫማዎችን የሰረቁት ተጠርጣሪዎች እየተፈለጉ ነው፡፡
በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ፔሩ የተፈጸመው የዝርፊያ ወንጀል የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
ሶስት ዘራፊዎች በማዕከላዊ ፔሩ ሁዋንካዮ ግዛት ጀኒን ከተማ የሚገኝ የስፖርት አልባሳት እና ጫማዎች መደብርን ሰብረው ይገባሉ።
በጥድፊያ ላይ የነበሩት ዘራፊዎች በካርቶን ታሽገው የተቀመጡ የተለያዩ ብራንድ ጫማዎችን ሰብስበው ይዘው ለመውጣትም ይጣደፋሉ።
220 ጫማዎችንም ይዘው ይሰወራሉ።
በቡጢ ፍልሚያ ቅራኔዎችን የምትፈታው የፔሩ መንደር
አስገራሚው ዜና ግን ዘራፊዎቹ ሰብረው ከገቡት መደብር ይዘው የወጡት ሁሉም የቀኝ እግር ጫማ የመሆናቸው ጉዳይ ነው።
ዘራፊዎቹ ስርቆቱን ከፈጸሙ በኋላ ሲወጡ በደህንነት ካሜራ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎም ፖሊስ ፍለጋውን ቀጥሏል።
የጄኒን ከተማ ፖሊስ አዛዡ ኤዱዋን ዲያዝ ፥ “የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሌባዎቹ መያዛቸው አይቀርም” ብለዋል።
ዘራፊዎቹ በመደብሩ ውስጥ ስርቆቱን ሲፈጽሙ ትተውት የሄዱት አሻራም እየተመረመረ በመሆኑ 220 የቀኝ እግር ጫማዎችን የሰረቁት ሶስት ሰዎች መያዛቸው እንደማይቀር ነው የተናገሩት።
የመደብሩ ባለቤት የቀኝ እግር ጫማዎቹ ካልተገኙ የግራ እግሮቹን ጫማዎች በተናጠል መሸጥ ስለማልችል የ13 ሺህ ዶላር ኪሳራ ይደርስብኛል ብሏል።
አስገራሚ ነው የተባለው ዜና ከተሰማ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
አንድ የትዊተር ተጠቃሚም “በርግጠኝነት ጫማዎቹን በግማሽ ዋጋ ለመሸጥ እያሰቡ ነው” የሚል አስተያየቱን ማጋራቱን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።