የነርቭ ህመምን ለማስታገስ በሚል የአገጭ ስፖርት ሲሰራ የነበረው ሰው ህይወቱ አለፈ
በቻይና ከሰባት ዓመት በፊት የጀርባ እና ነርቭ ህመምን ያስታግሳል የሚል የአገጭ ስፖርት እየተለመደ መጥቷል
የነርቭ ሕመም ያለበት የ52 ዓመት ቻይናዊ ይህን የአገጭ ስፖርት እየሰራ እያለ ህይወቱ አልፏል
የነርቭ ህመምን ለማስታገስ በሚል የአገጭ ስፖርት ሲሰራ የነበረው ሰው ህይወቱ አለፈ፡፡
የሩቅ ምስራቋ ቻይና ባህላዊ ህክምና በስፋት ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ከፈረንጆቹ በ2017 ጀምሮ ለነርቭ እና ጀርባ ህመም መፍትሔ ሆናል የተባለ ህክምና እየሰፋ መጥቷል፡፡
ይህ ባህላዊ ሕክምና የጀርባ እና ነርቭ ህመምን ለማስታገስ የሰውነት ክብደትን አገጭ ላይ በማድረግ በገመድ መንጠልጠል ነው፡፡
የዘመናዊ ህክምና ባለሙያዎች የአገጭ ስፖርት አደገኛ እና ተጨማሪ ጉዳትን ቢያስከትል እንጂ የሚፈውሰው አንዳች ነገር የለም እያሉ ቢያስጠነቅቁም ይን ህክምና የሚሞክሩ ዜጎች ቁጥር እየሰፋ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
በቻይናዋ ቸንግዲ በተሰኘች ከተማ ነዋሪ የሆነ የ57 ዓመት የጀርባ ህመምተኛ ይህን የአገጭ ስፖርት በመሞከር ላይ እያለ ህይወቱ ማለፉን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ግለሰቡ አገጩ ላይ ገመድ በማንጠልጠል ሙሉ የሰውነት አካሉን አየር ላይ በሚያደርግበት ወቅት ገመዱ ወደ አንገቱ በመሄድ ትንፋሽ አጥሮት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጎታል፡፡
ይሁንና አሁንም ይህ በአገጭ መንጠልጠል ለነርቭ እና ጀርባ ህመም ፈዋሽ ነው ብለው የሚያምኑ ቻይናዊያን ቁጥር ቀላል አይደለም የተባለ ሲሆን ግለሰቡ ገመዱን ሲያንጠለጥል የሰራው ስህተት ለሞት ዳርጎታል በማለት ላይ ናቸው፡፡
የህክምና ባለሙያዎች አሁንም መሰል ጥንቃቄ የጎደለው እና ፈዋሽነቱ በሳይንሳዊ መንገድ ያልተረጋገጠ የህክምና ዘዴ መጠቀም ጉዳቱ ያመዝናል ብለዋል፡፡