12 ጊዜ የመንጃ ፈቃድ ፈተና የወደቀው ጋናዊ አምሳያውን ለማስፈተን ሞክሯል
በቤልጂየም ነዋሪ የሆነው ጋናዊ እኔን ይመስላል ላለው ሰው ከፍሎ ፈተናውን ለማለፍ ያደረገው ጥረት ግን አልተሳካም
ሁለቱም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ቅጣት ተላልፎባቸዋል
በቤልጂየም ነዋሪ የሆነው ጋናዊው ሰርጌ በሀገር ቤት ያወጣው መንጃ ፈቃድ በአውሮፓዊቷ ሀገር አልጠቀመውም።
በደንብ መንዳት የሚችለው ሰርጌ በቤልጂየም መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ግን የጽሁፍ ፈተናው የማይቻል ይሆንበታል።
ለ12 ጊዜያት ሞክሮ አልሳካ ሲለውም አውጥቶ አውርዶ የተሻለ መፍትሄ ይሆነኛል ያለው እርሱን የሚመስልና ከዚህ ቀደም በቤልጂየም የመንጃ ፈቃድ ፈተና ተፈትኖ ያለፈ ሰው ፈልጎ እንዲፈተንለት ማድረግ ሆነ።
እናም ከአድካሚ ሙከራ በኋላ ጁሊያን የተባለ በመልክ ከእርሱ ጋር የሚመሳሰል ሰውን አገኘ።
የኮንጎ ዜግነት ያለው ጁሊያን ከሰርጌ ጋር የሚያመሳስለው ነገር ቢኖርም ቁርጥ እሱን የሚባል ግን አልነበረም።
በቤልጂየሟ ግራሞንት ከተማ ባቡር የሚያዘወትረው ሰርጌ ግን መንጃ ፈቃድ በእጁ ማድረጉን ትልቅ ትኩረት በመስጠት ለጁሊያን ገንዘብ ከፍሎና መታወቂያውን ሰጥቶ ወደ መፈተኛ ስፍራው ይልከዋል።
ቁጥጥሩ ላላ ያለ ነው ወዳሉት የመንጃ ፈቃድ ፈተና መውሰጃ ቦታ ለማምራት የተስማሙት ሰርጌ እና ጁሊያን ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ።
ጁሊያን ከሰርጌ የተቀበለውን መታወቂያ ሰጥቶ በቀላሉ እንደሚገባ ቢጠብቅም ተቆጣጣሪው አትኩሮ ተመለከተው። መታወቂያው ላይ የሚታየው ምስልና ከፊቱ የቆመው ሰው ልዩነትን ካረጋገጠ በኋላም በቁጥጥር ስር አዋለው። ፈተናውን እንዲወስድለት ጁሊያንን በገንዘብ ያግባባው ሰርጌም ካለበት ተይዞ ሁለቱም ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ጋናዊው ሰርጌ በአንድ አመት እስራት(ሌላ ወንጀል ካልፈጸመ ተፈጻሚ የማይሆን)፤ ተባባሪው የኮንጎ ዜጋ ጁሊያን ደግሞ የ200 ስአት የማህበረሰብ ነጻ አገልግሎት እንዲሰጥ ተወስኖባቸዋል ሲል ያስነበበው ኦዲቲ ሴንትራል ነው።