ፈተና ለመኮረጅ ጆሮው ውስጥ የብሉቱዝ ማዳመጫ በቀዶ ጥገና ያስተከለው ህንዳዊ ተማሪ ተያዘ
በፈተና ክፍል አነስተኛ ስልክና የብሉቱዝ ማዳመጫ መገኘቱን ተከትሎም የተፈታኞች የፈተና ወረቀት እንዲየር ተደርጓል
ከ11 ዓመት በፊት ወደ ኮሌጁ ገባው ተማሪው በተደጋጋሚ ፈተና ማለፍ አቅቶት ቆይቷል
በህንድ የሚገኝ አንድ የህክምና ተማሪ በቀዶ ህክምና ጆሮው ላይ አስተክሏል በተባለ አነስተኛ የብሉቱዝ ማዳመጫ አማካኝነት ፈተና ሲኮርጅ መያዙን ተከትሎ ጉዳዪ እየተጣራ መሆኑን የኮሌጁ ባለስልጣናት አስታውቀወል።
ከ11 ዓመት በፊት ወደ ኮሌጁ ገባው ተማሪው በተደጋጋሚ ፈተና ማለፍ እንዳቃተው የተነገረ ሲሆን፤ የተማሪው ባሳለፍነው ሰኞ ያደረገው ሙከራም የመጨረሻው ነበር ተብሏል።
የግል የህክምና ኮሌጅ ተማሪው በማህተማ ጋንዲ መታሰቢያ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ በሚሰጥ ፈተና ላይ ለመቀመጥ በመጣበት ጊዜ በለበሰው ሱሪ ውስጥ አነስተኛ ሲም የምትቀበል ስልክና የብሎቱዝ ማዳመጫ ይዞ መገኘቱን የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ሳንጃይ ዲክሲት ተናግረዋል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ተማሪው በሳላፍነው ሰኞ ከሌሎች 13 ተማሪዎች ጋር በመሆን የጄኔራል ሜዲስን ፈተናን ለመፈተን በተቀመጠበት መያዙንም ዲኑ አስታውቀዋል።
በተማሪው እጅ የተገኘው የጆሮ ማዳመጫ እና ስልክ እንዲነጠቅ ከተደረገ በኋላ የሌሎች ተፈታኞች የፈተና እና መልስ ወረቀቶችም መቀየራቸውንም ገልጸዋል።
በተማሪው እጅ ላይ የተገኘው የብሉቱዝ የጆሮ ማዳመጫው ከሰው የቆዳ ቀለም ጋር ተመሳስሎ የተሰራ እና ከአንገት በላይ ስፔሻሊቶች የቀዶ ህክምና በጆሮው ላይ የተተከለ መሆኑን መለየቱንም ኮሌጁ አስታውቋል።
አሁን ላይ የኮሌጁ የፈተና ኮሚቴ በተማሪው ላይ ምርመራ ማካሄድ መጀመሩን እና በእጁ ላይ የተገኘው መሳሪያም ለምርመራ መላኩን ያስታወቁት ዲኑ፤ ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳዩ ለፖሊስ የተላለፍ የሚለው ላይ ይወሰናል ብለዋል።