በ30 ቀናት 1 ሺህ እንቁላል የተመገበው ወጣት ምን ገጠመው?
በየቀኑ ከ30 እንቁላል በላይ መመገቡ ከ6 ኪሎግራም በላይ እንዲጨምር እንዳደረገው ተናግሯል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/273-174052-egg_167aca4e449af0_700x400.jpg)
እንቁላል በብዛት መመገቡ በደሙ ውስጥ የ"መጥፎ" ኮሊስትሮል መጠንን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም በተቃራኒው ሆኖ ተገኝቷል
በጃፓን መዲና ቶኪዮ ነዋሪ የሆነ ወጣት በወር 1 ሺህ እንቁላል መመገቡን አስታውቋል።
ጆሴፍ ኤቨርት የተባለው የሰውነቱን ቅርጽ በስፖርት የሚያዳብር ወጣት እንቁላል በብዛት መመገቡ ጡንቻውን ለመገንባት እንዳገዘው ተናግሯል።
በየእለቱን አመጋገቡንና ያሳየውን ለውጥ የሚያሳዩ ምስል በማጋራቱም በማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል ብሏል ዴይሊ ሜል በዘገባው።
በፍጥነት የሚሰለቸውን እንቁላል በጥብስ፣ በቅቅል እና በጥሪው ከሩዝ ጋር ሲበላ የከረመው ኤቨርት የ30 ቀናት አዲስ የአመጋገብ መንገድን ከመከተሉ በፊት ተገቢውን ምርመራ አድርጓል። ክብደቱ፣ በአራት አይነት ስፖርቶች ያለው ብቃት፣ የደም፣ ኮሊስትሮል እና ቴስቴስትሮን መጠን ሁሉ ተመዝግቧል።
ኤቨርት 1 ሺህ እንቁላል በ30 ቀናት ውስጥ ከተመገበ በኋላ 6 ኪሎግራም ጨምሮ ክብደቱ 84 ኪሎግራም ደርሷል። ክብደት የማንሳት አቅሙም በ20 ኪሎ ከፍ ማለቱን ነው ማረጋገጥ የተቻለው።
በሚያስደንቅ መልኩ በደሙ ውስጥ ያለው "መጥፎ" ኮሊስትሮል ሳይጨምር እንደውም የገንቢው ኮሊስትሮል መጠን ከፍ ብሎ መጥፎውን ለማስወገድ ረድቷል ይላል የምርመራ ውጤቱ።
ሌላው አስገራሚ ውጤት ከስትሮክ እና የልብ ህመም ጋር የሚያያዘውና በደም ውስጥ የሚገኘው "ትሪግሊሴሪድስ" የተሰኘ አደገኛ ስብ መጠኑ ዝቅ ብሎ የመገኘቱ ጉዳይ ነው።
በቀን ውስጥ ከ3 ሺህ 300 እስከ 3 ሺህ 700 ካሎሪ ያለው ምግብ ሲመገብ መቆየቱን ያወሳው ኤቨርት፥ ይህም ለወጣት ወንድ ከሚመከረው 2 ሺህ 500 ካሎሪ ከፍ ያለ መሆኑን ይገልጻል።
እንቁላል ከፍተኛ የፕሮቲን፣ ቫይታሚን፣ ካልሺየም፣ አይረን፣ ዚንክ እና ፖታሺየም ያለው በመሆኑ ከሶስት ወይም አራት እንቁላል በላይ መብላት እንደማይገባ ቆየት ያሉ ጥናቶች አሳይተዋል።
የእንቁላል ፍጆታን ማብዛት ለልብ ህመም ተጋላጭነትን ሊጨምር ይችላል የሚሉ ጥናቶችም ወጥተዋል።
በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ግን በእንቁላል አመጋገብ ላይ ገደብ የሚያስቀምጠው ጥናት ያረጀ ነው፤ የተመጣጠነ ምግብ የሚመገቡና ስፖርት የሚሰሩ ሰዎች በብዛት ቢመገቡ ችግር የለውም ማለታቸውንም የዴይሊ ሜል ዘገባ አመላክቷል።