ቀብሩ ላይ ምን ያህል ሰው እንደሚገኝ ለመታዘብ የውሸት መሞቱን ያወጀው ብራዚሊያዊ
ግለሰቡ የቀብር ስነ ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች ሁነቶችን በማዘጋጀት የሚተዳደር ሰው ነው
የ81 ዓመት ወላጅ እናቱ የልጃቸውን ሞት ሲሰሙ በልብ ህመም እንደተጠቁ ተነግሯል
ቀብሩ ላይ የሚገኘውን ሰው የውሸት መሞቱን ያወጀው ብራዚሊያዊ ውግዘትን እያስተናገደ ነው።
የ60 ዓመቱ ብራዚሊያዊ ባልታዛር ሌሞስ የቀብር ስነ ስርዓት ፕሮግራም በማዘጋጀት የሚተዳደር ግለሰብ ነው። በየጊዜው በሚያዘጋጃቸው የቀብር ስነ ስርዓቶች ላይ ብዙ ቅር የሚያሰኙ ነገሮችን ይታዘባል።
ቅር ከሚያሰኙ ክስተቶች መካከልም በስርዓተ ቀብር ላይ የሚገኙ የሰዎች ብዛት አንዱ እንደሆነበት ይገልጻል።
በአንዳንድ ስርዓተ ቀብሮች ላይ ሁለት ሰዎች ብቻ ይገኛሉ የሚለው ይህ ብራዚሊያዊ እሱ ቢሞት ስንት ሰው ይገኛል የሚለውን ለማወቅ ጉጉት እንዳደረበት ይገልጿል።
በዚህም መሰረት በፌስቡክ ገጹ ህይወቱ በድንገት ማለፉን የሚገልጽ መረጃ ማሰራጨቱን ተከትሎ በርካቶች ማዘናቸውን ይገልጻሉ።
የቀብር ስነ ስርዓቱ የሚፈጸምበትን ቀን ሳይቀር በተከታታይ ባሰራጨው መረጃ መሰረት ቤተሰቦቹ እና ወዳጅ ጓደኞቹ በተባለው ቀን ለስርዓተ ቀብሩ ይገኛሉ።
ይሁንና በመሀል ከሬሳ ሳጥን ውስጥ ብቅ ያለው ይህ ግለሰብ በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ ሰዎች የተለያዩ ስሜቶችን አስተናግደዋል።
ግለሰቡ አለመሞቱን ነገር ግን በቀብሬ ላይ እነማን ይገኛሉ የሚለውን ለማወቅ በሚል በውሸት ሞቻለሁ ማለቱን ይናገራል።
ከዚህ በኋላም ብዙዎች በግለሰቡ ድርጊት ማዘናቸውን የውሸት ስርዓተ ቀብሩን አቋርጠው ሲሄዱ ሌሎቹ ደግሞ አብረውት ፎቶ ተነስተዋል።
የ81 ዓመት ወላጅ እናቱ የልጃቸውን ሞት ሲሰሙ በልብ ህመም እንደተጠቁ እና ለስርዓተ ቀብሩ ሲሉ በዊልቸር በስፍራው መገኘታቸው ሲታይ በዚህ ግለሰብ ላይ ውግዘታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።