ሩሲያ በስህተት የራሷ ከተማ ላይ ቦምብ ጣለች
የሩሲያው ሱ-34 የጦር አውሮፕላን ከዩክሬን ድንበር 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለች ከተማን በቦምብ ደብድባል
ቤልጎሮድ የተሰኘችው ከተማ በስህተት ቦምብ የተተኮሰባት ሲሆን በጥቃቱ ሁለት ሰዎች ተጎድተዋል
ሩሲያ በስህተት የራሷን ከተማ በቦምብ ደበደበች።
ሩሲያ እና ዩክሬን ይፋዊ ጦርነት ከጀመሩ አንድ ዓመት ያለፋቸው ሲሆን ጦርነቱ በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ ነው።
ሁለቱም ሀገራት አዲስ ጥቃት ለመጀመር ሙሉ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ባለበት በዚህ ወቅት የሩሲያው ሱ-34 የጦር አውሮፕላን በስህተት ቦምብ ጥሏል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የጦር አውሮፕላኑ በስህተት ከዩክሬን ድንበር በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው ቤሎጎሮድ ከተማ ቦምብ ጥሏል።
የሩሲያ ፌደራል መንግሥት ስለ ጉዳዩ እስካሁን ምንም ያላለ ሲሆን የከተማዋ አስተዳዳሪ ግን በመኖሪያ ቤቶች ላይ የቦምብ ጥቃት መሰንዘሩን ተናግረዋል ።
በጥቃቱ በትንሹ ሁለት ሰዎች መጎዳታቸው እና የዜጎች መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች መጎዳታቸውን ተገልጿል።
በከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት ለጊዜው ጋብ ብሎ የቆየው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በቀጣዮቹ ሳምንታት ወደ ሙሉ ማጥቃት እንደሚገቡ ይጠበቃል ተብሏል።
ዩክሬን ለመልሶ ማጥቃት የሚረዷትን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ከብዙ ሀገራት እያሰባሰበች ትገኛለች።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ለዩክሬን የሚሰጡ የጦር መሳሪያዎች እንዲቆሙ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ሩሲያ የደህንነት ችግር ውስጥ ከገባች የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመጠቀም ትገደዳለች ሲሉም አስጠንቅቀዋል።