የዋግነር መሪ ፕሪጎዥን ሳይሞት አልቀረም መባሉን ተከትሎ የሀገራት መሪዎች ምን አሉ?
የአሜሪካው ፕሬዝዳት በይደን “አደጋው አላስገረመኝም፤ በሩሲያ ፑቲን ከጀርባ የሌበበት ብዙ ነገር የለም” ብለዋል
ዩክሬን “ፑቲን እምነት ያጎደለና መስመሩን ካለፈ ማንንም ይቅር እንደማይል ማሳያ ነው” ብላለች
በሩሲያ ባሳለፍነው ረቡዕ በደረሰ የአውሮፐላን አደጋ የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን ህይወት ሳያልፍ አልቀረም መባሉ ይታወቃል።
የዋግነር ሌሎች አመራሮችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የግል ጄት ከሞስኮ በስተሰሜን ተከስክሶ ሁሉም ተጓዦች ህይወታቸው አልፏል።
በዚህ በረራ ተጓዥ ከነበሩት ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ የፕሪጎዥንም ተካቷል መባሉን ተከትሎ ነው የዋግነር መሪው ህይወቱ አልፏል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ የሚገኙት።
ይህንን ተከትሎም የተለያዩ የዓለም ሀገራ መሪዎች አስተያየት ና መሰላቸውን መላ ምቶች በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
አሜሪካ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “በሩሲያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የዋግነር መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዥን ሞቶ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ብዙም አለስደነቀኝም” ብለዋል።
“ምን እንደተፈጠረ በትክክል አላውቅም፤ ግን አልገረመኝም” ያሉት ባይደን፤ “በሩሲያ ውስጥ ፑቲን ከጀርባ የሌበበት ብዙ ነገር የለም፤ ለአሁኑ የአውሮፕላን አደጋ ግን መልስ ለመስጠት በቂ እውቀት የለኝም” ብለዋል።
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አድሪያን ዋትሰን በሰጡት መግለጫ “በአውሮፕላ አደጋው የፕሪጎዥን ነነት ከተረጋገጠ ማንም አይደንቅም ” ብለዋል።
ፈረንሳይ
ፓሪስ ሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን ገድሏል ተብሎ በሚገመተው የአውሮፕላን አደጋ ላይ “ምክንያታዊ ጥርጣሬዎች” እንዳላት ተናግራለች።
የፈረንሳይ መንግስት ቃል አቀባይ ኦሊቪየር ቬራን ለፈረንሳይ 2 ቴሌቭዥን እንደተናገሩት፤ "የዚህን አደጋ ሁኔታ እስካሁን አናውቅም፤ አንዳንድ ምክንያታዊ ጥርጣሬዎች አለን” ብለዋል።
ዩክሬን
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ፤ “ዩክሬን ከአውሮፕላን አደጋው ጀርባ የለችም፤ ከአደጋው ጋር ተያይዞ ምንም ያደረግነው ነገር የለም፤ ከዚህ አደጋ ጋር ማን ግንኙነት እንዳለው ሁልም የገነዘባል” ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ረዳት ማይክያሎ ፖዶልያክ በበኩላቸው፤ “የአውሮፕላን አደጋው እምነት ለሚያጎል ማንኛውም ሰው ከክሬምሊን የተሰጠ ምክልት ነው” ያሉ ሲሆን፤ ድምዳሜ ላይ ከመድረስ ግን ውጤቱን መጠባበቅ ይሻላል ብለዋል።
“የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተፈጸመ ከሁለት ወራት በኋላ የፕሪጎዥን እና ሌሎች የዋግነር አመራሮች መወገድ ከ2024 ምርጫ በፊት ከፑቲን ለሩሲያ ልሂቃን የተላለፈ ምልዕክት ነው፤ በሩሲያ እምነትን ማጉደል ከሞት ጋር እኩል ነው" ሲሉም ማይክያሎ ፖዶልያክ ገልጸዋል።
ማይክያሎ ፖዶልያክ አክለውም “ፑቲን እምነት ያጎደለና መስመሩን ካለፈ ማንንም ይቅር እንደማይል ማሳያ ነው” ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጽ ባሰፈሩት ጽሁፍ አመላክተዋል።
የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ካጃ ካላስ፤ “ፑቲን ተቃዋሚዎቹን ያጠፋል፤ በዚህም ሊቃወሙት የሚፈልጉትንም ያስፈራራል” ሲሉ ተናግረዋል።
ፖላንድም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ “የፑቲን ጠላቶች የተፈጥሮ ሞት እንዲሞቱ አይፈቀድላቸውም” ብላለች።
ጀርመን ምንም አይነት አደጋ አልተፈጠረም ያለች ሲሆን፤ ብሪታኒያ ደግሞ ወደ ድምዳሜ መድረስ አይገባም ጉዳዩን እየተከታተልኩ ነው ስትል አስታውቃለች።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባሳለፍነው ረቡዕ ከሞስኮ በስተሰሜን ስለተከሰከሰው አውሮፕላን በሰጡት መግለጫም የዋግነር ቡድን መሪ ይቪግኒ ፕሪጎዥን በአውሮፕላኑ ውስጥ ስለመኖራቸው ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።
ፑቲን ስለ ዋግነሩ መሪ ሲናገሩም፤ “ይቪግኒ ፕሪጎዥን ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቼ ለረጅም ጊዜ አውቀዋለሁ፤ በህይወት አጋጣሚው አስቸጋሪ እጣ ፈንታ ያለው ሰው ነው፤ በህይወቱ ከባባድ ስህተቶችንም ሰርቷል፤ ለራሱ የሚፈልገውን ውጤት ለማግኘት ታግሏል” ብለዋል።
“እኔ እስከማውቀው ድረስ ፕሪጎዥን ከአፍሪካ ትናንት መመለሱን እና ከተወሰኑ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝቶ እንደነበረ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።