በራሱ ጭንቅላት ላይ ቀዶ ጥገና ያደረገው ሩሲያዊ
ግለሰቡ ህልምን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መሳሪያዎች ለማስገባት ነው የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን በማየት ቀዶ ጥገናውን ያደረገው
በጭንቅላቱ ላይ የደፈረው ግለሰብ በቀጣይ እስከሞት የሚያደርስ ጉዳት ሊያስተናድ እንደሚችል ተገልጿል
አወዛጋቢው ሩሲያዊ በራሱ ጭንቅላት ላይ ቀዶ ጥገና ማድረጉን አስታውቋል።
ማይክል ራዱጋ የተባለው ግለሰብ ህልምን መቆጣጠር የሚያስችል መሳሪያ ለማስገባት ነው ካዛስታን በተባለችው ከተማ በሚገኝ መኖሪያ ቤቱ በጭንቅላቱ ላይ የቀዶ ጥገና ያደረገው።
ምንም አይነት የህክምና ትምህርት የሌለው ራዱጋ ለረጅም ስአታት የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን በመመልከት ነው በራሱ ላይ አደገኛ ሙከራ ያደረገው።
ለማንም ሳያማክር ጭንቅላቱን ከፍቶ የፕላቲኒየም እና ሲልከን ኤሌክትሮድ (ህልምን ለመቆጣጠር እንደሚያስችሉ የታመነባቸው) ሲያስገባም ከ1 ሊትር በላይ ደም ፈሶታል ተብሏል።
ራዱጋ ምንም እንኳን የህክምና ዶክትሬት ባይኖረውም ከእንቅልፍ መዛባት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መቅረፍ ላይ ያተኮረ “ፌዝ ሪሰርች ሴንተር” የተሰኘ ተቋም አቋቁሟል።
በዚህ ማዕከልም መሰል ችግር ያለባቸው ሰዎችን የማማከር አገልግሎት እንደሚሰጥ እና በሩሲያ ተቀባይነትን እያገኘ መሄዱን ዴይሊ ሜል አስነብቧል።
የአዕምሮ ጤና ሀኪሞች ግን ግለሰቡ በአደገኛ ነገር እየቀለደ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና ትምህርት ክፍል የሚያስተምሩት አሌክስ ግሪን፥ ሩሲያዊው በራሱ ላይ ቀዶ ጥገና ሲያደርግ ብዙ ደም ስለፈሰሰው ስትሮክ አልያም ሌላ ለሞት ሊያደርስ የሚችል ህመም ሊገጥመው እንደሚችል ተናግረዋል።
ራሱ ራዱጋም ቀዶ ጥገናውን በጀመረ በ30 ደቂቃዎች ውስጥ ብዙ ደም ስለፈሰሰው ለሞት መቃረቡን አምኖ እንደነበር ተናግሯል።
ይሁን እንጂ አንዴ ጀምሬዋለውና ከግብ ሳላደርስ አላቆምም በሚል የጭንቅላት ቀዶ ጥገናውን ማጠናቀቁንና ሰውነቱን ተለቃልቆ ለ10 ስአት ስራውን መቀጠሉንም ይገልጻል። ይህም የቀዶ ጥገናውን ማንም እንዳያውቅበት ማድረጉን በማከል።
ከአምስት ሳምንታት በኋላ ወደ ሆስፒታል በማቅናት በጭንቅላቱ ውስጥ የከተታቸውን ነገሮች ካስወጣ በኋላም ያቋቋመው ተቋም መጥፎ ህልምን ለማስቀረት የሚያስችል ቀዶ ጥገና እናደርጋለን የሚል ማስታወቂያ መልቀቁም አስገራሚ ሆኗል።