በሰረቁት ክሬዲት ካርድ ሎተሪ የቆረጡት ሌቦች የ500 ሺህ ዩሮ እጣ እድለኛ ሆኑ
የክሬዲት ካርዱ ባለቤት ሌቦቹ ትኬቱን ይዘው የሚቀርቡ ከሆነ ገንዘቡን እንደሚያካፍላቸው ቃል ገብቷል

የፈረንሳይ የሎተሪ አስተዳደር ሎተሪውን በተሰረቀ ክሬዲት ካርድ መገዛቱን ካወቀ በኋላ የሽልማት ገንዘቡ እንዳይንቀሳቀስ አግዷል
ፈረንሳያዊው ዣን ዴቪድ ከሜድትራኒያን ባሕር 150 ኪሎሜትር በምትርቀው የፈረንሳይዋ ቱሉዝ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡
ግለሰቡ ከሁለት ሳምንት በፊት በከተማዋ ማዕከላዊ ስፍራ ከቆመ መኪናው ውስጥ ሁለት ሌቦች የጀርባ ቦርሳውን ሰርቀው ይሰወራሉ፡፡
መታወቂያ ፣ የክሬዲት ካርድ፣ መንጃ ፈቃድ እና ሌሎችንም እቃዎች ያስቀመጠበት የኪስ ቦርሳው በተሰረቀው ቦርሳ ውስጥ መሆኑን ተከትሎ ባአፋጣኝ ለፖሊስ እና ለባንክ አሳውቆ በክሬዲት ካርዱ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ያሳግዳል፡፡
ይሁን እና ግለሰቡ የሚገለገልበት ባንክ የክሬዲት ካርዱን አገልግሎት ከማቋረጡ በፊት ቦርሳውን የሰረቁት ሌቦች ወደ አንድ ሱፐር ማርኬት ጎራ በማለት ሲጋራ እና ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሎተሪዎችን ሲገዙ በደህንነት ካሜራ ታይተዋል፡፡
ሌቦቹ ከቆረጧቸው የሚፋቁ የሎተሪ ትኬቶች መካከል አንደኛው ትኬት አንደኛ እጣ 500 ሺ ዩሮ የሚያሸልም ሆኗል፡፡
ሎተሪው የተገዛው በተሰረቀው ግለሰብ ስም በሚገኝ ክሬዲት ካርድ በመሆኑ ሌቦቹ ትኬቱን ወስደው የሽልማት ገንዘቡን መቀበል አልቻሉም፡፡
ይህን ያወቀው የክሬዲት ካርዱ ባለቤት ዣን ዴቪድ ታድያ ሌቦቹ ሎተሪውን ይዘው የሚቀርቡ ከሆነ ክስ እንደማይመሰርትባቸው እንዲሁም የሽልማትን ገንዘቡን እኩል እንደሚያካፍላቸው ቃል ገብቷል፡፡
ጄን ዴቪድ ከፈረንሳዩ አርቲኤል ሬድዮ ጋር ባደረገው ቆይታ “እነሱም ያለ እኔ ገንዘብ ሎተሪውን ሊቆርጡ አይችሉም ነበር፤ እኔም የሽልማት ገንዘቡን ትኬቱን ካላገኘሁ ማውጣት አልችልም ስለዚህ የሎተሪ ባለስልጣኑ ገንዘቡን ከሚወስደው በስምምነት እንድንካፈለው ጥሪ አቀርባለሁ” ብሏል፡፡
ቦርሳውን የሰረቁት ግለሰቦች ገንዘቡን ለመቀበል ወደ ሎተሪ ባለስልጣኑ ቢያቀኑ ግዢው የተፈጸመው በሌላ ሰው ስም በመሆኑ በማጭበርበር ወይም በስርቆት ወንጀል ለእስራት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡
በሱፐር ማርኬት የደህንነት ካሜራ ውስጥ ትኬቱን ሲገዙ የታዩት ግለሰቦች የጎዳና ተዳዳሪዎች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ የተናገረው ዣን ዴቪድ፤ “ይህ ገንዘብ የሁላችንንም ህይወት መቀየር የሚያስችል በመሆኑ ቀነ ገደቡ ሳይጠናቀቅ ብንገናኝ መልካም ነው” ብሏል፡፡
የሚፋቁ የሎተሪ ትኬቶች እጣ ከተቆረጠበት ቀን ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ የትኬቱ ባለቤት ቀርቦ የሽልማት ገንዘቡን የማይወስድ ከሆነ ገንዘቡ ወደ ሎተሪ ባለስልጣኑ ተመላሽ ይሆናል፡፡
የፈረንሳይ የሎተሪ አስተዳደር ሎተሪውን በተሰረቀ ክሬዲት ካርድ መገዛቱን ካወቀ በኋላ የሽልማት ገንዘቡ እንዳይንቀሳቀስ አግዷል፤ ነገርግን የክሬዲት ካርዱ ባለቤት ትኬቱን ይዞ ከቀረበ ገንዘቡን ለመስጠት በህግ ይገደዳል፡፡