አውሮፓ ያለአሜሪካ ድጋፍ ራሱን ከጥቃት መከላከል የሚችልበት አቅም ይኖረው ይሆን?
አህጉሩ ራሱን መካላከል የሚችልበትን አቅም ይገነባ ዘንድ በአመት ከ260 ቢሊየን ዶላር በላይ ለመከላከያ ወጪ መመደብ አለበት ተብሏል

በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ማስቆም ሂደት ከዋሽንግተን ጋር ልዩነት ውስጥ የሚገኙት አውሮፓውን የደህንነት ዋስትናቸውን ከአሜሪካ ጥገኘነት ለማላቀቅ እየተሯሯጡ ነው
አውሮፓ ያለአሜሪካ ድጋፍ ራሱን ከጥቃት መከላከል የሚችልበት አቅም ይኖረው ይሆን?
በሰሜን አትላንትኪ ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና በሌሎች የድጋፍ ማዕቀቦች ከአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ እና ጥበቃ የሚደረግለት አውሮፓ ራሱን ችሎ ለመቆም አዳዲስ ፖሊሲዎችን ማሳለፍ እንደሚኖርበት እየተነገረ ይገኛል፡፡
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ወደ ስልጣን መምጣት እና በውጭ ጉዳይ የሚከተሉት ፖሊሲ ለየት ማለት አህጉሩ ከደህንነት እና ዋስትና ጋር በተገናኘ ራሱን ችሎ ለመቆም በተለያዩ መንገዶች እየመከረ ነው፡፡
በትላንትናው ዕለት ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት አውሮፓ ያለአሜሪካ ድጋፍ የደህንነት ስጋት ጥያቄውን መመለስ የሚያስችል አቅም እንዳለው ቢገልጽም፤ ይህን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ መመደብ እና ከአሁን ጀምሮ ፍኖተ ካርታ መንደፍ እንደሚኖርበት አሳስቧል፡፡
የጥናቱ ውጤት እንደሚያመላክተው አውሮፓ ያለአሜሪካ ድጋፍ ደህንነቱን ለማስጠበቅ በየዓመቱ 261.6 ቢሊዮን ዶላር ለመከላከያ ማውጣት ይኖርበታል።
ይህ ከአውሮፓ ህብረት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 1.5 በመቶ ጋር እኩል የሆነ ወጪ አህጉሩ 300 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን በማሰባሰብ ከሩሲያ እና ከሌሎች አካላት ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን መከላከል የሚያስችለውን አቅም የሚፈጥርለት ነው፡፡
በ”በሩጄል እና ኬል የአለም ኢኮኖሚ ተቋም” የወጣው ጥናት አውሮፓ የፋይናንስ አቅም ቢኖረውም በአህጉሪቱ ያለው የመከላከያ ቅንጅት ደካማ መሆን ፈተና ሊሆን እንደሚችል ጠቅሶ የቅንጅት አሰራር እንዲዘረጋ መክሯል፡፡
ከዚህ ባለፈም የመከላከያ ወጪው ከሀገር ውስጥ ምርት እድገት አንጻር እስከ አራት በመቶ ከፍ እንዲል ከዚህ ውስጥ ግማሹ በጋራ ብድር የሚሸፈን ሲሆን ግማሹ ደግሞ ሀገራቱ ራሳቸው እንዲሸፍኑ ምክረ ሀሳቡን አስቀምጧል፡፡
ሀገራቱ ራሳቸውን መከላከል የሚያስችላቸውን አቅም እንዲፈጥሩ እና የመከላከያ ወጪያቸውን እንዲያሳድጉ ከትራምፕ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እየደረሳቸው ሲሆን አህጉሩ አሜሪካን ለድህንነቱ ሃላፊ አድርጎ ከመወስድ እንዲታቀብም ማስጠንቀቂያ ደርሶታል፡፡
በጀርመን ቻንስለር ምርጫ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙት ፍሬድሪክ ሜሪዝ በአሜሪካ የኔቶ አባል ሆኖ መዝለቅ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ በበኩላቸው እስከመጪው ሰኔ ድረስ ሁሉም የኔቶ አባላት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 በመቶ የሚሆነውን የመከላከያ ወጪ ሙሉ በሙሉ እንዲያሟሉ ቀነ ገደብ ሰጥተዋል።
የ”በሩጄል እና ኬል የአለም ኢኮኖሚ ተቋም” ጥናት ሞስኮ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ወታደራዊ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ ያሳደገች ሲሆን፤ ለዩክሬን ጦርነት ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ማሰባሰቧን ፣ የታንክ እና የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን ምርት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሯን ጠቅሷል።
አውሮፓ ከሩስያ የሚሰነዘርበትን ጥቃት ለመቋቋምለ 50 ተጨማሪ ብርጌዶች 1400 አዲስ የጦር ታንኮች እና 2 ሺህ ተዋጊ ተሽከርካሪዎች እንደሚያስፈልጉትም አመላክቷል፡፡