ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ሶስት መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታወቀች
ሩሲያ ጦርነቱ በሚቆምበት ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር መነጋገር ብትጀምርም፣ በምስራቅ ዩክሬን ድል እያስመዘገበች ትገኛለች

በዩክሬን ላይ "ልዩ ያለችውን ዘመቻ" በ2022 የከፈተችው ሩሲያ ዶኔስክንና ሌሎች በከፊል የያዘቻቸውን ሶስት ግዛቶች የራሷ ግዛት አድርጋ አውጃለች
የሩሲያ ኃይሎች በምስራቅ ዩክሬኗ ዶኔስክ ግዛት የሚገኙ ናዲቭካ፣ኖቮሲልካና ኖቮቸረቱቬት የተባሉ ሶስት መንደሮችን መቆጣጠራቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው እለት አስታውቋል።
ሩሲያ ሶስት አመታት ያስቆጠረው ጦርነት በሚቆምበት ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር መነጋገር ብትጀምርም፣ በምስራቅ ዩክሬን አዝጋሚ ነገርግን ቀጣይ የሆነ ድል እያስመዘገበች ትገኛለች።
በዩክሬን ላይ "ልዩ ያለችውን ዘመቻ" በ2022 የከፈተችው ሩሲያ ዶኔስክንና ሌሎች በከፊል የያዘቻቸውን ሶስት ግዛቶች የራሷ ግዛት አድርጋ አውጃለች። ይህ የሩሲያ እርምጃ በተባበሩት መንግስት ድርጅት ጉባኤ ላይ በአብዛኞቹ የአለም ሀገራት ውግዘት ማስተናገዱ ይታወሳል።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት መጠነሰፊ ድጋፍ ሲያደርግላት የነበረው የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር በምርጫ መሸነፍ የአሜሪካን ድጋፍ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
አሜሪካ ለዩክሬን ያደረገችው ድጋፍ የሚቆጫቸው የወቅቱ ፕሬዝደንት ትራምፕ ዩክሬን 500 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ብርቅ ማዕድናት ለአሜሪካ ማቅረብ አለባት ሲሉ ተደምጠዋል።
የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ለማስቆም ቃል በገቡት ትራምፕ የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደር ከሩሲያ ጋር ንግግር ማድረግ ጀምሯል። ከሰሞኑ በአሜሪካና በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተመሩ ሁለት የልኡካን ቡድኖች ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ በሳኡዲ አረቢያ ሪያድ መክሯል።
ሁለቱ ሀገራት አቋርጠውት የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማደስም ተስማምተዋል።
አውሮፓውያንና ፕሬዝደንት ዘለንስኪ በዚህ ስብሰባ አለመሳተፋቸው ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ የገቡ ሲሆን የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት በጉዳዩ ላይ ለመሞከር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ነበር። በፕሬዝዳንት ትራምፕና በዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ መካከል ያለው ክፍተት የሰፋ ሲሆን ትራምፕ ዘለንስኪን ምርጫ የማያካሄድ "አምባገነን"ሲሉ ተችተዋቸዋል።