ለ32 አመት ብቻቸውን የኖሩት ጣሊያናዊ ወደ ከተማ ህይወት በተመለሱ በ3 አመት ውስጥ ሞቱ
ማውሮ ሞራንዲ የቡዴሊ ደሴት ብቸኛ ነዋሪ ሆነው ከሶስት አስርት አመታት በላይ አሳልፈዋል
አዛውንቱ ስግብግብ ሰዎችን እና ፖለቲከኞችን ለመሸሽ ነበር የብቸኝነት ህይወትን የመረጡት
ከ30 አመት በላይ ብቻቸውን የኖሩት ጣሊያናዊ ወደ ከተማ ህይወት በተመለሱ በሶስት አመት ውስጥ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ።
ማውሮ ማራንዲ የተባሉት አዛውንት በፈረንጆቹ 1989 ነበር በደቡባዊ ሳርዲና ቡዴሊ ወደተባለች ደሴት ያቀኑት።
የቀድሞው የስፖርት መምህር "ስግብግብ ሰዎችን እና የጣሊያን የፖለቲካ ህይወትን ለመሸሽ" እና ከስልጣኔ ለመራቅ በሚል ከጓደኞቻቸው ጋር የጀመሩት ጉዞ ቡዴሊ እንዳደረሳቸው በ2018 ለቢቢሲ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረው ነበር።
ጓደኞቻቸው ለመመለስ ሲወስኑ ሞራንዲ ግን በጡረታ የሚወጡትን የቡዴሊ ደሴት ጠባቂ ተክተው ለመቆየት ተስማምተው ለ32 አመታት ብቸኛው የደሴቷ ነዋሪና ጠባቂ ሆነው ቆይተዋል።
የከተማ ህይወት በቃኝ ያሉት አዛውንት የደሴቷን ቆሻሻ እያጸዱ ጉብኝት ለሚያደርጉ ታዳጊዎችም ስለአካባቢ ጥበቃ እያስተማሩ ሰላማዊ ህይወት ሲመሩ መቆየታቸውንም አውስተዋል።
ይሁን እንጂ በተለያየ ጊዜ ከደሴቷ እንዲወጡ በባለስልጣናት ጫና ሲደረግባቸው ነበር።
በ2020 የ"ላ ማዳሌና" ብሄራዊ ፓርክ ፕሬዝዳንት ፋብሪዚዮ ፎኔሱ፥ ማራንዲ በሚኖሩበት ቤት ላይ ህገወጥ ማሻሻያ አድርገዋል በሚል ከሰዋቸው እንደነበር ሲኤንኤን አስታውሷል። መኖሪያ ቤታቸው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት እንደ ሬዲዮ ጣቢያ ሲያገለግል የቆየ ነበር።
የቡዴሊ ደሴትን የአካባቢ ጥበቃ ትምህርት ማዕከል የማድረግ ውጥን የነበራቸው ማራንዲ ከደሴቷ እንዳይወጡ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ፊርማ ቢያሰባስቡላቸውም ወደማይፈልጉት የከተማ ህይወት ከመመለስ አልታደጋቸውም።
በ2021 በ "ላ ማዳሌና" ደሴት ባለአንድ መኝታ አፓርትመንት ውስጥ መኖር እንዲጀምሩ የተደረገ ሲሆን፥ ባለፈው አመት በድንገት ከወደቁ በኋላ ታመው ሳሳሪ በተባለች ከተማ ህክምና ሲደረግላቸው ቆይቷል።
ከሰሞኑም በሰሜናዊ ጣሊያን በምትገኘው የትውልድ ከተማቸው ሞዴና በ85 አመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል።
ሞራንዲ በ2021 ከዘጋርዲያን ጋር ባደረጉት ቆይታ ከቡዴሊ ደሴት ከወጡ በኋላ ህይወት እንደከበዳቸው ተናግረው ነበር። "በፊት በረጅም ዝምታ ውስጥ ነበርኩ፤ አሁን ግን የማያቆም ረብሻ ውስጥ እገኛለሁ" ማለታቸው ለትውስታ ተነስቷል።