ዩናይትድ በጊዜያዊ አሰልጣኙ ሩድ ቫኒስትሮይ መሪነት ቼልሲን ያሸንፍ ይሆን?
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ በኦልድትራፎድ ቼልሲን ያስተናግዳል
ሰማያዊዮቹ በፕሪሚየር ሊጉ ከሜዳቸው ውጪ ቀያይ ሰይጣኖቹን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፉት ከ11 አመት በፊት ነው
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ ከቼልሲ ዛሬ ምሽት 1 ስአት ከ30 ይገናኛሉ።
ሩበን አሚሪም እስኪተው ድረስ ዩናይትድን በጊዜያዊነት እያሰለጠነ የሚገኘው ሩድ ቫን ኒስትሮይ ባለፈው ረቡዕ በካራባዋ ካፕ ያስመዘገበውን ድል ለመድገም ቡድኑን እየመራ በኦልትራፎርድ ይገኛል።
ቫን ኒስትሮይ በሀሙሱ የቅድመ ጨዋታ መግለጫው በተጫዋቾች ጉዳት ዙሪያ መረጃ ባይሰጥም በዛሬው ጨዋታ አንቶኒ፣ ሃሪ ማጓየር፣ ኮቢ ማይኖ፣ ማሶን ማውንት፣ ሉክ ሻው እና ሌኒ ዮሮ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ አይጠበቅም ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
- ማንችስተር ዩናይትድ ሩብን አሞሪምን ቀጣዩ የቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አረጋገጠ
የቼልሲው አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ በበኩላቸው ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች ለፍልሚያው ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ከዩናይትድ በውሰት ቼልሲን የተቀላቀለው ጆርዳን ሳንቾ ዋና ክለቡን አይገጥምም።
የማንቸስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ የርስ በርስ ጨዋታ ውጤቶች
- ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ባደረጋቸው ያለፉት 11 ጨዋታዎች በቼልሲ አልተሸነፈም (አምስቱን አሸንፎ በስድስቱ ነጥብ ተጋርቷል)። ዛሬ የሚያሸንፍ ከሆነም ከ1957 ወዲህ በኦልትራፎርድ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ቼልሲን የረታበት ሆኖ ይመዘገባል።
- የለንደኑ ክለብ ቼልሲ ባለፈው ሚያዚያ ዩናይትድን 4 ለ 3 ማሸነፉ ይታወሳል።
- ሰማያዊዮቹ በኦልትራፎርድ ቀያይ ሰይጣኖቹን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፉት በግንቦት 2013 ነው፤ ብቸኛዋን የድል ጎልም ዩዋን ማታ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።
- የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በአቻ ውጤት በመጠናቀቅ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ቀዳሚው ሆኖ ተመዝግቧል፤ 64 ጊዜ ተጫውተው 26ቱ ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ
- ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ በዘጠኝ ጨዋታዎች 11 ነጥቦችን ሰብስቦ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፤ ይህም በዘጠኝ ጨዋታዎች ያስመዘገበው ዝቅተኛው ውጤት ሆኗል፤ በ2019/20 በ9 ጨዋታዎች ካስመዘገበው በአንድ ነጥብ ዝቅ ያለ ነው።
- ዛሬ በቼልሲ ከተሸነፈ ከ1986/87 የውድድር አመት በኋላ በ10 ጨዋታ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበበት ይሆናል፤ ይህ ውጤት(1986/87) ሮበን አትኪንሰንን በሰር አሌክስ ፈርጉሰን እንዲተኩ ማስገደዱ ይታወሳል።
- ኤሪክ ቴን ሀግ በአሰልጣኝነት ቆይታው ካስተናገዳቸው 27 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሽንፈቶች ሰባቱ ከ90 ደቂቃ በኋላ በተቆጠሩ ጎሎች የተመዘገቡ ናቸው።
- ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ12 ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልቻለም፤ ሌስተርን 5 ለ 2 ባሸነፉበት የካራባዋ ዋንጫ ሁለትት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ቼልሲ
- ሰማያዊዮቹ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 የውድድር አመት በዘጠኝ ጨዋታዎች 17 ነጥብ ሰብስበው በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
- ካለፉት 24 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች (14 አሸንፈው በሰባቱ አቻ ተለያይተዋል) ሶስቱ የመጨረሻ ሽንፈታቸው ከአርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ጋር በተገናኙባቸው ጨዋታዎች የተመዘገበ ነው።
- በሊጉ የሚያሰልፏቸው ተጫዋቾች አማካይ እድሜ 23 አመት ከ206 ቀናት ነው፤ ይህም ክለቡን ከተፎካካሪዎቹ አንጻር በወጣቶች የተሞላ አድርጎታል።
- ኮል ፓርመር በ42 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ለሰማያዊዮቹ 29 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ ከ50 በታች ጨዋታ አድገው ለክለቡ 30 ጎሎች ያስቆጠሩት ጂሚ ፍሎይድ ሃሰልባይንክ (41 ጨዋታ) እና ዲያጎ ኮስታ (48 ጨዋታ) ናቸው።
- ኒኮላስ ጃክሰን ባለፉት 14 የቼልሲ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በ14 ጎል የሆኑ ኳሶች በቀጥታ ተሳትፎ አድርጓል፤ 10 ጎሎችን አስቆጥሮ አራት ለግብ አመቻችቶ አቀብሏል።