ማንችስተር ዩናይትድ ሩብን አሞሪምን ቀጣዩ የቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አረጋገጠ
ከ10 ጨዋታዎች ሰባቱን የማሸነፍ ምጣኔ እንዳለው የሚነገርለት አሰልጣኝ ከህዳር 11 ጀምሮ ቡድኑን መምራት ይጀምራል
ሩብን አሞሪም በስፖርቲንግ ሊዝበን በነበረው ቆይታ ቡድኑ ከ19 አመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሏል
ማንቸስተር ዩናይትድ ሩብን አሞሪምን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አረጋገጠ፡፡
ከመጪው ሳምንት ቀጥሎ በሚመጣው ሰኞ ህዳር 11 ከስፖርቲንግ ሊዝበን ወደ ኦልትራፎርድ የሚዘዋወረው የ39 አመቱ ፖርቹጋላዊ እስከ ሰኔ 2027 ድረስ የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።
ኤሪክ ቴን ሃግ ሰኞ እለት ከተሰናበቱ በኋላ በጊዜያዊነት አሰልጣኝነቱን የተረከበው የቀድሞ የዩናይትድ አጥቂ ሩድ ቫን ስትሮይ በክለቡ የሚቀጥሉት ሶስት ጨዋታዎችን ይመራል።
በ2013 የሰር አሌክስ ፈርጉሰን የ26 አመታት የስልጣን ቆይታ ካበቃ በኋላ ዩናይትድ ቋሚ አስልጣኝ ሲሾም አሞሪም ስድስተኛው ነው።
ክለቡ ባወጣው መግለጫ “ሩበን በአውሮፓ እግር ኳስ ውስጥ ካሉ ወጣት አሰልጣኞች መካከል ከፍተኛ ደረጃ የተሰጠው አሰልጣኝ ነው” ብሏል።
በአውሮፓ እግር ኳስ ስሙ እያደገ የመጣው ወጣቱ አስልጣኝ በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ሊቨርፑል ፣ ቼልሲ እና በዌስትሀም ተፈላጊነት ነበረው፡፡
የፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ በመግለጫው እንዳረጋገጠው ማንቸስተር ዩናይትድ የአሞሪምን ኮንትራት ውል ማፍረሻ 11ሚሊየን ዩሮ ለመክፈል መስማማቱን አረጋግጧል።
የቀድሞው የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አማካይ ተጫዋች ሩብን አሞሪም የአስልጣኝነት ስራውን የጀመረው በ2018 ካሳፒያ የተባለ ቡድንን በማሰልጠን ነው፡፡
በዛው ክረምት የብራጋን ቢ ቡድን በ11 ጨዋታዎች ላይ መምራት የቻለ ሲሆን፤ ቀጥሎም ዋናውን ቡድን በመረከብ ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ብራጋ ከ65 አመታት በኋላ ከሜዳው ውጭ እንዲያሸነፍ አስችሏል፡፡
ከ2021 ጀምሮ ስፖርቲንግ ሊዝበንን ተረክቦ ማሰልጠን የጀመረው ሩብን ቡድኑ አምስት ዋንጫዎችን እንዲያነሳ ማድረግ ችሏል፡፡
ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ የፖርቹጋል ሊግ ዋንጫ ከመሆናቸውም በላይ ስፖርቲንግ ከ19 አመት በኋላ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ በማስቻል ዋና ሰው ነው፡፡
በዘንድሮው አመት የፖርቹጋል ሊግ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ሽንፈት ያልገጠመው ስፖርቲንግ በሩብን አስለጣኝነት አራት አመታት ባደረጋቸው 237 ጨዋታዎች 514 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
በዚህም 34 ጨዋታዎችን አሸንፎ 33 ከመሸነፉ በቀር በሁሉም ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡
በአማካይ 71.7 በመቶ ወይም ከአስር ጨዋታዎች 7 ጨዋታዎችን የማሸነፍ ምጣኔ ያለው ቡድን መገንባትም ችሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ቡድኑ በአማካይ በጨዋታ 2.17 ግቦችን የሚስቆጥር ሲሆን የሚቆጠርበት ግብ 0.18 ብቻ እንደሆነ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
አሰልጣኙ 3-4-3 ወይም 3-4-2-1 በማጥቃት እና በኳስ ቁጥጥር ላይ ላይ የተመሰረተ ጨዋታ እንደሚከተል የሚነገርለት ሲሆን ወጣቶችን በማብቃት እና አቅማቸውን በማጎልበት ልዩ ችሎታ አለው ሲል የኢንግሊዙ ሚረር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
አሞሪም እ.ኤ.አ. ህዳር 24 ከአለም አቀፍ እረፍት በኋላ ፕሪምየር ሊግን አዲስ ከተቀላቀለው ኢፕስዊች ጋር በሚደረገው ጨዋታ ማንችስተርን ለመጀመርያ ጊዜ ይመራል፡፡
ማክሰኞ በቻምፒየንስ ሊግ ስፖርቲንግ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በሜዳው ሲገጥም በተጨማሪም አሞሪም የመጨረሻውን ጨዋታ በህዳር 10 በሊጉ ከቀድሞ ክለቡ ብራጋ ጋር የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ሩብን አሞሪም በሳምንት ጊዜ ውስጥ በፕሪምየር ሊግ 14ኛ እና በዩሮፓ ሊግ ሠንጠረዥ ከ36 ቡድኖች 21ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝው ማንችስተር ዩናይትድ ማሰልጠን ይጀምራል፡፡