በ92 አመታቸው የወለዱት አውስትራሊያዊ በድንቃድንቅ መዝገብ መስፈራቸውን ያውቃሉ?
አሜሪካዊው የኦስካር አሸናፊ ተዋናይ ሮበርት ዲኒሮ በዚህ ሳምንት ሰባተኛ ልጁን በ79 አመቱ ማግኘቱን አስታውቋል
በህንድ፣ እስራኤል እና አሜሪካ ከ90 አመት በላይ የሆናቸው አዛውንቶች ልጅ መውለዳቸውን ማሳወቃቸው አወዛጋቢ ቢሆንም በታሪክ ተመዝግቧል
አሜሪካዊው ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ሮበርት ዲኒሮ በዚህ ሳምንት ሰባተኛ ልጁን ማግኘቱን አስታውቋል።
የኦስካር ሽልማት አሸናፊው በ79 አመቱ ልጅ የመውለዱ ዜና ከተሰማ በኋላም ወንዶች ልጅ ለመውለድ እድሜ አይገድባቸውም የሚለውን ጉዳይ አጠናክሮታል።
በአሜሪካ እና ብሪታንያ ወንዶች ልጅ የሚያገኙበት አማካይ እድሜ 33 እና 30 አመት ነው።
ምንም እንኳን እስካሁን ወንዶችንን አባት ከመሆን የሚያስቆመው የእድሜ ጣሪያን ማወቅ ባይቻልም እድሜያቸው የገፋ ሰዎች በሚወልዷቸው ህጻናት ላይ የሚከሰተው የጤና ችግር አሳሳቢ መሆኑን ጥናቶች አመላክተዋል።
በእርጅና ዘመናቸው ልጅ የወለዱ አባቶች እነማን ናቸው?
ጀምስ ስሚዝ
በአሜሪካ ኢሊኖይስ ነዋሪ የነበሩት ጀምስ ስሚዝ በፈረንጆቹ 1951 (በ101 አመታቸው) የ38 አመት እድሜ ከነበራት ባለቤታቸው ልጅ ማግኘታቸውን ገልጸው ነበው።
በ1849 እንደተወለዱ የሚናገሩት ጀምስ ስሚዝ እድሜ ጉዳይ ግን አጠራጣሪ እንደነበር በታሪክ ተጽፏል።
በተለያዩ ሰነዶች ላይም ከሚጠቅሱት አመት 15 አመት ዘግይተው መወለዳቸው ተጠቅሷል።
በዚህም ቢሆን ጀምስ ስሚዝ በ86 አመታቸው ልጅ በመውለድ በእርጅና ዘመናችው ልጅጅ ካገኙ አባቶች መካከል ተጠቃሽ ሆነዋል።
ራምጂት ራግሃቭ
ህንዳዊው ራምጂት ራግሃቭ በፈረንጆቹ 2010 የመጀመሪያ ወንድ ልጁን ሲያገኝ እድሜው 94 አመት ነበር።
ጡረተኛው ራምጂት ከሁለት አመት በኋላ በ2012 የ54 አመት ጎልማሳ ከሆኑት ባለቤታቸው ሻኩንታላ ሁለተኛ ወንድ ልጃቸውን ማግኘታቸው ተዘግቧል።
ይሁን እንጂ የራምጂት ራግሃቭ ትክክለኛ እድሜን የሚያመላክት ሰነድ ማግኘት አልተቻለም።
ለስ ኮሊ
በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስማቸው የሰፈረው አዛውንቱ አባት አውስትራሊያዊው ለስ ኮሊ ናቸው።
ኮሊ በ92 አመታቸው ከሶስተኛ ሚስታቸው 9ኛ ልጃቸውን ማግኘታቸው ተረጋግጦ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
አዛውንቱ በ90 አመታቸው በፈረንጆቹ 1991 በትዳር አጋር አገናኝ ድረገጽ ላይ ካገኙዋት ሚስታቸው ነው 9ኛ ልጃቸውን የወለዱት።
ለስ ኮሊ 100 አመት ሊደፍኑ አራት ወራት ሲቀራቸው በሳንባ ምች በሽታ ህይወታቸው ማለፉም ተነግሯል።
ሞሃመድ አል አደም
በእስራኤል ሄብሮን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ማሃሙድ አል አደም በ92 አመታቸው 13ኛ ልጃቸውን በማግኘት ዝርዝሩን ተቀላቅለዋል።
የታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ እንደሚያሳየው አደም በ50 አመት ከሚበልጧት አበር የተሰኘች ሚስታቸው ነው 13ኛ ልጃቸውን ያገኙት።
አዛውንቱ የመጀመሪያ ሚስታቸውን በሞት ካጡ በኋላ ካገቧት አበር ያገኟትን ልጅ “ታማራ” የሚል ስም ሰጥተዋታል፤ የህጻኗ ስም “ቴምር” ወይም “የቴምር ዛፍ” የሚል ትርጓሜም አለው።
ጁሊዮ ኢግለሲያስ ፑጋ
የታዋቂው ሙዚቀኛ ጁሊዮ ኢግለሲያስ አባት፤ የነኢንሪኮ፣ ጁሊዮ (ጁኒየር) እና ቻቤቲ ኢግለሲያስ አያት ዶክተር ጁሊዮ ኢግለሲያስ ፑጋ የቅድመ ወሊድ ክትትል ስፔሻሊስት ነበሩ።
ይሁን እንጂ ዶክተር ጁሊዮ ኢግለሲያስ ከህምክና እውቀታቸው ይልቅ ሴት አውልነታቸው ይበልጥ እውቅና አስገኝቶላቸዋል።
የቴሌግራፍ ዘገባ እንደሚያሳየው ኢግለሲያስ “ፓፑቺ” የሚል ቅጽል ስም ነበራቸው፤ በስፔንኛ “ትንሹ አባት” እንደማለት ነው።
ጁሊዮ ኢግለሲያስ ፑጋ በፈረንጆቹ 2005 ህይወታቸው ከማለፉ አምስት ቀናት በፊት (በ90 አመታቸው) 42 አመት እድሜ ከነበራቸው ባለቤታቸው ልጅ ለማግኘት እየተጠባበቁ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።