ፑቲንን በቁጥጥር ስር ማዋል ከሩሲያ ጋር ጦርነት ማወጅ ነው - ራማፎሳ
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሞስኮ በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝዳንቷን መያዝ እንደ ጦርነት አዋጅ እመለከተዋለሁ ማለቷን ተናግረዋል
የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ በቀጣይ ወር በጆሃንስበርግ ይካሄዳል
ደቡብ አፍሪካ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጆሃንስበርግ በቁጥጥር ስር ማዋል ከሞስኮ ጋር ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል አሉ።
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሩሲያም በስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንቷን መያዝ እንደ ጦር አዋጅ እወስደዋለሁ ማለቷን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በቀጣይ ወር በጆሃንስበርግ በሚካሄደው የብሪክስ (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ) ጉባኤ መታደም እንደሚፈልጉ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው መሆኑና ደቡብ አፍሪካም ፈራሚ ሀገር እንደመሆኗ ፑቲንን በቁጥጥር ስር አውላ አሳልፋ እንድትሰጥ ትገደዳለች።
የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አስተዳደር ፑቲንን በቁጥጥር ስር አውሎ ችግር ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ የትናንቱ የፕሬዝዳንቱ መግለጫ ያመላክታል።
የሀገሪቱ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ “ዲሞክራቲክ አሊያንስ” ግን የራማፎሳ አስተዳደር ፑቲንን እንዲይዝ ጉዳዩን በፕሪቶሪያ ወደሚገኝ ፍርድ ቤት በመውሰድ ጫና እያደረገ ይገኛል።
ራማፎሳ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የጽሁፍ ምላሽ ፕሬዝዳንት ፑቲንን መያዝ የዩክሬን ጦርነትን ለማርገብ ሀገራቸው እያደረገች የምትገኘውን ጥረት እንደሚያሰናክል ነው ያብራሩት።
ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የሩሲያ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንቶች ያነጋገሩ ሲሆን፥ ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳም ሞስኮ በጆሃንስበርጉ ጉባኤ ፑቲንን መያዝ ምን አንድምታ እንዳለው የሰጠችውን ማብራሪያ በመጥቀስ ሀገራቸው የአለማቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ለማስጸም እንደምትቸገር ገልጸዋል።
“ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት የሚያመራ ድርጊት መፈጸም ከህገመንግስታችን ይቃረናል” ማለታቸውንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በቀጣይ ወር በሚካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ስለመሳተፍ አለመሳተፋቸው በቅርብ ቀናት ውስጥ መግለጫ ይሰጣል ተብሏል።