ኖርዌጂያዊው ጄንስ ስቶልትንበርግ የፊታችን ጥቅምት ስልጣናቸውን ለማርክ ሩት ያስረክባሉ ተብሏል
ማርክ ሩት የኔቶ ዋና ጸሃፊ ተደርገው ተመረጡ፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አውሮፓን እና አሜሪካንን ከየትኛውም ጥቃት ለመከላከል በሚል ነበር የተመሰረተው፡፡
በዓለማችን ካሉ ወታደራዊ ተቋማት መካከል በጥንካሬው ቀዳሚ ነው የሚባልለት ኔቶ በአሜሪካ የበላይነት ይመራል፡፡
31 አባል ሀገራትን ያቀፈው ኔቶ ዋና ጸሃፊ በየአምስት ዓመቱ ከአባል ሀገራቱ የተውጣጣ መሪ በምርጫ ወደ ሀላፊነት የማምጣት ስርዓት አለው፡፡
የሩሲያ እና የኔቶ ወታደራዊ አቅም ሲነጻጸር ምን ይመስላል?
በዚህም መሰረት ላለፉት አምስት ዓመታት የኔቶ ዋና ጸሃፊ የሆኑት ኖርዌጂያዊው ጄንስ ስቶልትንበርግ የፊታችን ጥቅምት ስልጣናቸውን ለተተኪያቸው የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማር ሩት ያስረክባሉ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ላለፉት 14 ዓመታት ኔዘርላንድን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ማርክ ሩት እና ፓርቲያቸው ከወራት በፊት በተካሄደ የህግ አውጪ ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ተሸንፈዋል፡፡
ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን ዋነኛ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ድጋፎችን የሚያደርገው ኔቶ ከሩሲያ ጋር ወደ ቀጥታ ጦርነት የመግባት ስጋት እንዳለበት የወቅቱ የቃል ኪዳኑ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልትንበርግ በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ማርክ ሩት ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ዋሸንግተን እንደሚያቀኑ የሚጠበቅ ሲሆን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደማቅ አቀባባል እንደሚያደርጉላቸው ተገልጿል፡፡
የኔቶ አባል የሆኑት ቱርክ እና ሀንጋሪ የማርክ ሩትን ዋና ጸሃፊነት ተቃውመው የነበረ ቢሆንም ዘግይተው በተደረጉ ውይይቶች ግን ሀገራቱ ተቃውሟቸውን አንስተዋል ተብሏል፡፡