ኔቶ ወደ ዩክሬን ወታደሮች የመላክ እቅድ የለኝም አለ
ጀርመንና ፖላንድም ወደ ኬቭ ወታደሮቻቸውን እንደማይልኩ ያሳወቁ ሲሆን፥ ሞስኮ የማስጠንቀቂያ መግለጫ አውጥታለች
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት የሰጡት አስተያየት ከክሬምሊን እስከ ብራሰልስ መነጋገሪያ ሆኖ ውሏል
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ዩክሬን ወታደሮችን ለመላክ እቅድ እንደሌለው አሳወቀ።
የአሜሪካ መራሹ ወታደራዊ ጥምረት ኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ ፥”የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ አለማቀፍ ህጉ ይፈቅድላቸዋል” ብለዋል።
ድጋፉ ወታደሮችን መላክን ሊጨምር እንደሚችል ያነሱት ዋና ጸሃፊው ይሁን እንጂ በጉዳዩ ዙሪያ አባል ሀገራቱ ምክክር አድርገው ስምምነት ላይ እንዳልደረሱ ለአሶሼትድ ፕረስ ተናግረዋል።
ኔቶ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን ለመላክ የ31ዱንም ሀገራት ድጋፍ ይፈልጋል።
የወታደራዊ ጥምረቱ አባል ሀገራት ለኬቭ ቢሊየን ዶላሮችን የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ቢልኩም አንድም ወታደር የመላክ ፍላጎት የላቸውም ተብሏል። ውሳኔው ኔቶን ወይም አባል ሀገራቱን ኒዩክሌር ከታጠቀችው ሩሲያ ጋር በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ስለሚያስገባቸው።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ትናንት በፓሪስ በተካሄደ ጉባኤ ላይ ያደረጉት ንግግር ግን ከክሬምሊን እስከ ብራሰልስ መነጋገሪያ ሆኖ ውሏል።
ማክሮን “የሩሲያ መሸነፍ ለአውሮፓ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው፤ ለዚህም ወታደሮችን መላክን ጨምሮ የትኛውንም እርምጃ መውሰድ ይገባል” ብለዋል።
የምዕራባውያን ድጋፍ መዘግየት ሞስኮ ድል እንድትቀዳጅና ከዩክሬን አልፋ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጦርነት እንድታውጅ ያደርጋል በሚል ወታደሮችን የመላኩ ጉዳይ እንዲታሰብበት መጠየቃቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
በዩክሬን ጦርነት ያስከፈተኝ የኔቶ “ቅጥ ያጣ መስፋፋት ነው” የምትለው ሞስኮ የማክሮንን ንግግር በቀላሉ አልመለከተችውም።
ኔቶ ወደ ዩክሬን ወታደሮችን ከላከ ከወታደራዊ ጥምረቱ ዋነኛ መሪ አሜሪካም ሆነ ከሌሎች አባል ሀገራቱ ጋር በቀጥታ ጦርነት መጀመሩ አይቀርም ብለዋል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ።
በአውሮፓ ፈርጣማ ወታደራዊ አቅም የገነቡት ጀርመን እና ፖላንድም ወደ ዩክሬን ወታደሮቻችን አንልክም የሚል መግለጫ አውጥተዋል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ በፓሪሱ የዩክሬን ጉባኤ የኔቶም ሆነ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ወደ ዩክሬን ምድር ወታደሮችን ከመላክ ለመቆጠብ ነው የተስማማነው ሲሉ ከማክሮን የተለየ አስተያየት ሰጥተዋል።
ዋነኛው የጦርነት ገፈት ቀማሽ ዩክሬን በበኩሏ ለፓሪስ፣ ብራሰልስ እና ሞስኮ የቃላት ልውውጥ ቁብ ሳትሰጥ ምዕራባውያን ቃል የገቡላትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ በፍጥነት እንዲያቀርቡላት እየተማጸነች ነው።