ኔቶ የሩሲያን “ሴራ” ለማክሸፍ እየሰራሁ ነው አለ
የወታደራዊ ጥምረቱ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ፥ ሞስኮ በኔቶ አባል ሀገራት ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም ጥረት እያደረገች ነው ብለዋል
የኔቶ አባል ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በብራሰልስ ምክክር ማድረግ ጀምረዋል
ሩሲያ በኔቶ አባል ሀገራት ላይ እየፈጸመች ያለውን “ጸብ አጫሪ ድርጊት” ለማስቆም እየሰራን ነው አሉ የኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ።
ኔቶ የደህንነት መረጃዎችን በፍጥነት ለማጋራት፣ ዋና ዋና መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅና የሩሲያ ደህንነቶች እንቅስቃሴን በጥብቅ በመከታተል ረገድ ከአባል ሀገራቱ ጋር ቅንጅቱን እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።
የሞስኮ “ሴራ” የኔቶ አባል ሀገራት ለኬቭ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀንሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ነው ዋና ጸሃፊው በብራሰልስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ያብራሩት።
ስቶልተንበርግ ሩሲያ በኔቶ አባል ሀገራትና አጋሮች ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈጸምና ሀሰተኛ መረጃዎችን የማሰራጨት ዘመቻ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ተናግረዋል።
ፖላንድ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በቅርቡ ሞስኮ የሳይበርና ሌሎች የሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ለማድረስ ሙከራ ማድረጓን መግለጻቸው ይታወሳል።
የላቲቪያ የመከላከያ ሚኒስትር አንድሪስ ስፕሪድስም፥ “ይህን (የሳይበር ጥቃት ሙከራ) በላቲቪያ አይተናል፤ ሁሉም የኔቶ አባል ሀገራት ሙከራው ሊያጋጥማቸው ይችላል” ብለዋል።
ሩሲያ ዜጎቿን በህገወጥ መንገድ ወደ ላቲቪያ በማስገባት ጥቃት ለማድረስ እንደምትንቀሳቀስም ነው ያነሱት።
ፖላንድም ለሩሲያ ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸውን ሶስት ሰዎች ባለፈው ግንቦት ወር በቁጥጥር ስር ማዋሏ ይታወሳል።
የጀርመን የደህንነት አገልግሎትን ጠቅሶ ዶቼ ቬለ እንዳስነበበው የሀገሪቱ የግንባታ ሰራተኞች በቅርቡ በኔቶ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ፈንጂዎችን አግኝተዋል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እነዚህ በወታደራዊ ጥምረቱ አባል ሀገራት ላይ የሚደረጉ “ጸብ አጫሪና የሰርጎ ገብ ጥቃት ሙከራዎች” ሀገራቱ ለዩክሬን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያቋርጡ ለማድረግ ያለሙ መሆናቸውን ያምናል።
ዛሬ በብራሰልስ በተጀመረው የአባል ሀገራቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባም ይህን የሞስኮ ድርጊት ማስቆም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ የንስ ስቶልተንበርግ ተናግረዋል።
ሞስኮ ለኔቶ እና አባል ሀገራቱ ወቀሳ ምላሽ ባትሰጥም ኔቶ ወደ ምስራቅ የሚያደርገውን መስፋፋት እንዲያቆምና ለኬቭ የሚያደርገው ድጋፍ መቀጠልም ከወታደራዊ ጥምረቱ ጋር ጦር እንደሚያማዝዛት ደጋግማ ገልጻለች።
አሜሪካ እና ብሪታንያን ጨምሮ የኔቶ አባል ሀገራት ለኬቭ የላኩት የጦር መሳሪያ ግዛቷን ዘልቆ ገብቶ ጥቃት እንዲያደርስ ከፈቀዱም የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ልትጠቀም እንደምትችል አስጠንቅቃለች።