ከባሌ ጋር ወሲብ ባለመፈጸሜ ትዳሬ ሊፈርስ አይገባም ያለችው ሴት በፍርድ ቤት ክርክር አሸነፈች
የችሎት ክርክር ሂደቱ ሲካሄድ ከ10 ዓመት በላይ እንደወሰደ ተገልጿል
ዳኞች በትዳር ውስጥ ወሲብ መፈጸም ግዴታ ሊሆን አይገባም ሲሉ ፍርዱን ወስነዋል ተብሏል
ከባሌ ጋር ወሲብ ባለመፈጸሜ ትዳሬ ሊፈርስ አይገባም ያለችው ሴት በፍርድ ቤት ክርክር አሸነፈች።
በአጭሩ ኤችደብሊው በሚል ስም የምትጠራው ሴት ፈረንሳዊት ስትሆን ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ነች።
ባንድ ወቅት ከባሏ ጋር ወሲብ መፈጸም እንደማትፈልግ መናገሯን ተከትሎ ባልየው ትዳሩ እንዲፈርስ ጉዳዩን ይዞት ወደ ፍርድ ቤት ያመራል።
ባለትዳሮቹ በፍቅር በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ አራት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን አንዱ ልጃቸው የአካል ጉድለት ያለበት በመሆኑ እናትየው ጊዜዋን ይህንን ልጅ በመንከባከብ ስለምታሳልፍ እና ድካም እንደሚሰማት ገልጻለች።
በዚህ እና ባልየው አደረሰብኝ በምትላቸው ጥቃቶች ምክንያት ወሲብ የመፈጸም ፍላጎት የለኝም የምትለው ሚስትየዋ ትዳሯ ግን እንዲፈርስ እንደማትፈልግ ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።
" ወሲብ አለመፈጸሜ እንደ ጥፋት ታይቶ ትዳሬ ሊፈርስ አይገባም" በሚል ተቃውሞ በፍርድ ቤት የተከራከረችው ይህች ሴት በወቅቱ በክርክር ተረታም ነበር።
የፈረንሳይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ባስተላለፈው የፍርድ ውሳኔ " በትዳር ውስጥ ወሲብ መፈጸም ግዴታ ነው፣ ይህ ባልሆነበት ትዳሩ ይፍረስልኝ ተብሎ የቀረበው አቤቱታ ትክክለኛ በመሆኑ ትዳሩ ፈርሷል" ሲልም ውሳኔ አስተላልፈዋል።
በውሳኔው ቅር የተሰኘችው ይህች እናትም ብራስልስ ለሚገኘው በአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቋን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ፍርድ ቤቱም ከሁለት ቀናት በፊት በዋለው ችሎት በትዳር ውስጥ ወሲብ መፈጸም ግዴታ ሊሆን አይገባም፣ አመልካቿም ለትዳሩ መፍረስ ተጠያቂ ልትሆን አይገባም ሲል የቀድሞውን ፍርድ ውድቅ አድርጓል።
የባለትዳሮቹ የፍርድ ክርክር ከ20 ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን ሚስትየዋም አሁን ላይ የ69 ዓመት አዛውንት ሆነዋል።
በፈረንሳይ ለየት ያሉ የፍርድ ቤት ክርክሮች መሰማት የተለመደ ሲሆን ከአንድ ወር በፊት ሚስቱን በ50 ወንዶች ያስደፈረው ባል የ20 ዓመት እስር ተላልፎበታል።