የስፔን ፖሊስ በወሲብ ባርነት ላይ የነበሩ 25 ሴቶችን ነጻ አወጣ
ሴቶቹ ከኮሎምቢያ ቆንጆ ስራ ትሰራላችሁ ተብለው ተታለው የመጡ ኮሎምቢያዊያን ናቸው ተብሏል
እነዚህ የስፔን ወንበዴዎች በማላጋ በተደራጀ ወንጀል የሚፈጽሙ እንደነበሩ ተገልጿል
የስፔን ፖሊስ በወሲብ ባርነት ላይ የነበሩ 25 ሴቶችን ነጻ አወጣ፡፡
የስፔን ብሔራዊ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ተገደው በወሲብ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ ተደርገው የነበሩ ሴቶችን ከወንበዴዎች ማስለቀቁን አስታውቋል፡፡
ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ ሴቶቹ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ተታለው ከደቡብ አሜሪካዊቷ ኮሎምቢያ የመጡ ናቸው ተብሏል፡፡
በርካታ የወንጀል ቡድን አባላት ያሉት ይህ የወንበዴዎች ስብስብ ከፍተኛ ገንዘብ እና ሰንሰለት ያለው ነው የተባለ ሲሆን ማላጋ ከተማን ዋና ማዕከላቸው እንዳደረጉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ፖሊስ እንደገለጸው በዚህ ከተማ በሰራው ዘመቻ 25 ሴቶች ከነበሩበት የግዳጅ ወሲብ ባርነት ወይም ንግድ ነጻ የወጡ ሲሆን 11 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል፡፡
ሩሲያ ለምን የሚሳኤል ጠበብቶቿን በሀገር መክዳት ወንጀል ጠረጠረች?
እንዲሁም 1 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም ኮኬይን የተሰኘው አደገኛ እጽ እና 150 ሺህ ዩሮ ጥሬ ገንዘብ መያዙን አስታውቋል፡፡
እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ከኮሎምቢያ ወደ ስፔን የውበት ሳሎን እና ሌሎች ስራዎችን ትሰራላችሁ ተብለው በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት መምጣታቸው ተገልጿል፡፡
እነዚህ ሴቶች የትራንስፖርት እና ሌሎች ወጪዎቻቸው በአሰሪዎቻቸው እንደሚሸፈኑ ተነግሯቸው ከመጡ በኋላ ወጪውን ራሳችሁ ክፈሉ በማለት ተገደው ወደ ወሲብ ንግድ እንዲገቡ፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ወሲብ ከደንበኞች ጋር እንዲፈጽሙ እና ሌሎች አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ሲፈጸሙባቸው እንደቆዩ በዘገባው ለይ ተገልጿል፡፡
ፖሊስ አክሎም እነዚህ ወንበዴዎች ሴቶችን አታለው በማምጣት አስገድደው ወዳዘጋጇቸው የወሲብ ንግድ ስፍራዎች በማስገባት በዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ገቢ ሲያገኙ እንደነበርም አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ 500 ሴቶች በነዚህ ወንበዴዎች ሰለባ እንደሆኑም ፖሊስ አስታውቋል፡፡