በጀርመን የሚገነባው ይህ የሀይል ማመንጫ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዩሮ በጀት ተመድቦለታል
የአረብ ኢምሬቱ ማስዳር ኩባንያ በጀርመን የንፋስ ሀይል ለማመንጨት ስምምነት ፈረመ።
የተባበሩት አረብ ኢምሬቱ ማስዳር የታዳሽ ሀይል ማመንጫ ጣቢያ በአውሮፓ የንፋስ ሀይል ማመንጫ ጣቢያ ለመገንባት ስምምነት ፈርሟል።
ማስዳር ኩባንያ ስምምነቱን ከጀርመኑ ኢበርድሮላ ኩባንያ ጋር በስፔን ማድሪድ የተፈራረመ ሲሆን ከ2024 ጀምሮ ግንባታው እንደሚጀመር ተገልጿል።
ማስዳር ኩባንያ ዋና መቀመጫውን በተባሩት አረብ ኢምሬት በማድረግ በታዳሽ ሀይል ልማት የሚሰራ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነው።
ኩባንያው በባልቲክ ባህር ጫፍ ላይ ከሚነሳው ንፋስ 476 ሜጋ ዋት ሀይል ለማመንጨት እና ለጀርመን ለመሸጥ ተስማምቷል።
ኩባንያው በሚያመነጨው የንፋስ ሀይል ለ20 ዓመታት በሰዓት 64 ሜጋዋት ሀይል ለማቅረብ መስማማቱም ተገልጿል።
የሀይል ስምምነት ፊርማውን የማስዳር ኩባንያ ስራ አስኪያጅ መሀመድ ጃሚል አል ራማሂ እና የኢቤርድሮላ ኩባንያ ሊቀመንበር ኢግናሲዮ ጋላን በማድሪድ ፈርመዋል።
ስምምነቱ አረብ ኢምሬት ለታዳሽ ሀይል ለሰጠችው ትኩረት እንደማሳያ ይወሰዳል የተባለ ሲሆን የሀይል ማመንጫ ጣቢያው 475 ሺህ አባወራዎችን የሀይል ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
በማስዳር እና ኢበርድሮላ ኩባንያዎች ትብብር የሚገነባው ይህ የሀይል ማመንጫ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅን 800 ሺህ ቶን ካርበንን እንደሚያስቀር ተገልጿል።
የሀይል ማመንጫው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ይደረግበታል የተባለ ሲሆን የጀርመኑ ኢበርድሮላ ኩባንያ የሀይል ማመንጫውን ማስተዳደር፣ ጥገና ማድረግ እና ሌሎች የአስተዳድር ስራዎችን ያከናውናል ተብሏል።
ማስዳር ኩባንያ ከዚህ ሀይል ማመንጫ ላይ የ49 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል የተባለ ሲሆን ቀሪው ማለትም 51 በመቶው ደግሞ የኢበርድሮላ ድርሻ እንደሆነ ተገልጿል።