አሜሪካ በአማራ ክልል እየተባባሰ ያለው ግጭት እንዳሳሰባት ገለጸች
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በስልክ ተወያይተዋል
ብሊንከን ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በፖለቲካዊ ንግግር መፍታት እንደሚገባት ተናግረዋል
አሜሪካ በአማራ ክልል “እየተባባሰ ያለው ግጭት” አሳሳቢ ነው አለች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
በዚህም ብሊንከን ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮቿን በፖለቲካዊ ንግግር መፍታት እንደሚገባት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደነገሯቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ማቲው ሚለር ባወጡት መግለጫ አንስተዋል።
አሜሪካ ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረው የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል።
ሌላው ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በስልክ ውይይታቸው የመከሩበት የሁለት አመቱን የትግራይ ጦርነት ለማስቆም በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ነው።
ዋሽንግተን የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ድጋፏን እንደምትቀጥል ብሊንከን ማረጋገጣቸውን ያስታወቁት ማቲው ሚለር፥ በስምምነቱ አፈጻጸም ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር መምከራቸውን ጠቁመዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ባወጣቸው መግለጫዎች “በትግራይ የጥይት ድምጽ መጥፋቱ”ን እና የተቋረጡ አገልግሎቶች ዳግም መመለሳቸውን በማድነቅ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስና ሌሎች መሰረታዊ የስምምነቱ መሰረታዊ ጉዳዮች አፈጻጸም እንዲፋጠን መጠየቁ ይታወሳል።
ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ በትግራይ ክልል የሚገኙ የታጠቁ ሃይሎች እንዲወጡ መጠየቁም አይዘነጋም።
ከሶስት ቀናት በፊት ሁለት አመት የደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት እና አፈጻጸሙ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሃት ሲያወዛግብ ቆይቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በስልክ ሲወያዩ በወቅታዊ የምስራቅ አፍሪካ ውጥረት ዙሪያም ተነጋግረዋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ መሻከሩ ይታወቃል።
ሉአላዊነቴ ተደፍሯል ያለችው ሞቃዲሾ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከማባረር አንስቶ ሌሎች እርምጃዎችን ወስዳለች።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን ሰጣ ገባ በንግግር መፍታት እንደምትፈልግ ስትገልጽ ቆይታለች።
ባለፈው ሳምንት ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፥ “ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት የማይናወጥ ፍላጎት አላት” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ይህን ለማሳካት ሰላማዊ መንገድን እንደምትመርጥና ገፍቶ ለሚመጣ ሃይል ግን ምላሽ እንደምትሰጥ ማስጠንቀቃቸውም አይዘነጋም።