በማዕከላዊ ጃፓን ከባድ ርዕደ መሬት ተከሰተ
ቶኪዮ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 6 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት ሱናሚ ስለሚያስከትል ዜጎቿ እንዲጠነቀቁ አሳስባለች
ደቡብ ኮሪያ እና ሩሲያም የውቅያኖስ ማዕበል ወይም ሱናሚ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል
በማዕከላዊ ጃፓን በዛሬው እለት ከባድ ርዕደ መሬት ተከስቷል።
በ90 ደቂቃዎች ውስጥ በሬክተር ስኬል ከ4 ነጥብ በላይ ሆነው የተመዘገቡ 21 የርዕደ መሬት ክስተቶች መመዝገባቸውንም የሀገሪቱ የሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።
በርዕደ መሬት መለኪያ 7 ነጥብ 6 ሆኖ የተመዘገበው አደጋ ከፍተኛ የባህር ማዕበል ወይም ሱናሚ ሊያስከስት እንደሚችል በመጥቀስም ዜጎች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል።
ኢሽካዋ በተባለው አካባቢ እስከ 5 ሜትር ከፍታ ያለው ሱናሚ ሊከሰት እንደሚችል በመገለጹም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በአዲስ አመት በዓል ከቤታቸው ለመውጣት ተገደዋል ነው የተባለው።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ “ካላችሁበት ውጡ” የሚል ጽሁፍ በተደጋጋሚ በማሳየት ላይ ሲሆን፥ በማህበራዊ ሚዲያዎች ርዕደ መሬቱ ያደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምስሎች እየተለቀቁ ነው።
ለርዕደ መሬት ተጋላጭ የሆነችው ጃፓን ሱናሚ ይከሰታል በሚል ዜጎቿን ስታስጠነቅቅ ከ2011 በኋላ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
በማዕከላዊ ጃፓን አውራ ጎዳናዎችን ዝግ ያደረገውና ከ36 ሺህ በላይ ሰዎችን ከኤሌትሪክ ያቆራረጠው አደጋ በሰዎች ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት አልተገለጸም።
የጃፓን መንግስት ቃል አቀባይ ዮሺማ ሃያሺ ተጨማሪ የርዕደ መሬት አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ በምስራቃዊ የባህር ዳርቻዋ ጋንግዎን ግዛት ዛሬ ሱናሚ ሊከሰት እንደሚችል ገልጻለች።
ሩሲያም ቭላዲቮስቶክ እና ናክሆድካ በተባሉት የወደብ ከተሞች ከባድ የውቅያኖስ ማዕበል ወይም ሱናሚ ሊከሰት ስለሚችል ነዋሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቧን ታስ ዘግቧል።
በሰሜን ምስራቃዊ ጃፓን ከ13 አመት በፊት በተከሰተው ከባድ ርዕደ መሬትና ባስከተለው ሱናሚ ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።